ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያዊያን ስጦታ የሆነውን አትሌቲክስ ስፖርትን ልትጠብቁትና ልትንከባከቡት ይገባል - ዶክተር ስቴፈን ቤርሞን

አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2011 ለኢትዮጵያዊያን ስጦታ የሆነውን የሩጫ ስፖርት ልትጠብቁትና ልትንከባከቡት ይገባል ሲሉ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች  ማህበር የጤናና ሳይንስ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ዶክተር ስቴፈን ቤርሞን ተናገሩ ። ዶክተር ስቴፈን  በ22ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ''በእግር ኳስ ብዙም ውጤት ያላችሁ አይመስልኝም ''  ብለዋል። አያይዘውም በሩጫ ውድድር ደግሞ በዓለም መድረክ ውጤታማ የሆኑ በርካታ አትሌቶች እንዳሉና እራሳቸውንና ቤተሰባቸውና ከመጥቀም አልፈው በኢንቨስትመንትም  ሀገራቸውን እየጠቀሙ መኖራቸውን አውቃለሁ ብለዋል። ለአብነትም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሆቴልና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማራውን ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገብርስላሴን አንስተዋል። ሌሎችም አትሌቶች በተመሳሳይ ስራዎች ላይ በመሰማራት ሀገራቸውን እየጠቀሙ ናቸው ብለዋል። ይህን እድል የፈጠረውን የሩጫ ስፖርት መጠበቅና መንከባከብ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ስፖርቱን የበለጠ ለማሳደግ የታዳጊዎች ስልጠና ላይ ማተኮር እንደሚገባና የእድሜ ማጭበርበር ችግርም ሊፈታ እንደሚገባው ነው የተናገሩት። የእድሜ ማጭበርበር  ችግር በዓለም ዓቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ስራ ላይ  ትልቅ ችግር እየሆነ መምጣቱንም በማውሳት። በመሆኑም ለአትሌቶች ፓስፖርቶች ሲሰጡ አሰራሮችን ማየትና ችግሩን መፍታት ይገባልም ብለዋል። ስፖርቱን ለማሳደግ ሌላው ትልቅ ስራ መሆን ያለበት የአበረታች መድኃኒት መከላከል እንደሆነ ገልጸው በኢትዮጵያ በኩል በዚህ ላይ ጥሩ መሻሻሎች እንዳሉና ስራዎቹ ግን ተጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም