አየር ኃይልን በዘመኑ የአቪየሺን ቴክኖሎጂ ለማስታጠቅ እየተሰራ ነው...ብርጋዴል ጀነራል ይልማ መርዳስ - ኢዜአ አማርኛ
አየር ኃይልን በዘመኑ የአቪየሺን ቴክኖሎጂ ለማስታጠቅ እየተሰራ ነው...ብርጋዴል ጀነራል ይልማ መርዳስ
ድሬዳዋ ጥቅምት 25/2011 የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሀገሪቱን ከማንኛውም ጥቃት በአስተማማኝ መንገድ መጠበቅ እንዲችል በዘመኑ የአቪየሺን ቴክኖሎጂ የማስታጠቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢፌድሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል ይልማ መርዳስ አስታወቁ። በድሬዳዋ የሚገኘው የምስራቅ አየር ኃይል ምድብ በመሰረታዊ የበረራ ትምህርት ያሰለጠናቸውን 12 ዕጩ አብራሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን በሶማሊያ ፀረ አልሸባብ ዘመቻ ላይ ታላቅ ገድል ፈጽመው ለተመለሱ የአየር ኃይል አባላትም ደማቅ አቀባበል ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የምስራቅ አየር ኃይል ምድብ ላለፉት ሁለት ዓመታት በኤፍ-260 መሰረታዊ የመጀመሪያ ደረጃ የበረራ ትምህርት በንድፈ ሃሳብና በተግባር ያሰለጠናቸውን 8 ኢትዮጵያውያንና 4 የቻድ ዜጎችን ትናንት አስመርቋል፡፡ በምርቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአየር ኃይል ከፍተኛ አመራሮች፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማንና የካቢኔ አባላት በሶማሊያ ፀረ- አልሸባብ ዘመቻ ለተሳተፉና አኩሪ ተግባር ለፈጸሙ አባላት ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡ በምረቃና አቀባበል ሥነስርአቱ ላይ የኢፌድሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንደተናገሩት የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ ደረጃ የሚጠብቅና በማንኛውም ግዳጅ ተልዕኮውን በአጭር ጊዜና በአነስተኛ መስዋዕት ከግብ ማድረስ የሚችል ዘመናዊ ሠራዊት ለመገንባት እየተሰራ ነው፡፡ " የሀገሪቱ የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት ነቅቶ ለመጠበቅ ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮ የተሸከመው አየር ኃይልን ዘመኑ ከሚጠይቀው የኢቬየሽን ቴክኖሎጂ ጋር ለማዘመን መጠነ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ነው " ብለዋል፡፡ እንደብርጋዴር ጄኔራል ይልማ ገለጻ የምስራቅ አየር ኃይል ምድብ በተለያዩ ግዜያት በሶማሊያ የተሰጠውን ተልዕኮ በአስተማማኝ ብቃት መፈጸሙ አቅሙን እያጎለበተ ስለመምጣቱ አንድ ማሳያ ነው። "በቅርቡ በነሃሴ ወር 2010 ዓ.ም በሶማሊያ በተሰጠው ተልዕኮ ባከናወነው ፀረ- አልሻባብ ዘመቻ አኩሪ ተግባር መፈፀሙ የጥንካሬውን ማሳያው ነው" ብለዋል፡፡