ቀጥታ፡

የአማራ ክልልን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት ውጤት እያስገኙ ናቸው-ርዕሰ መስተዳድር ገዱ

ባህር ዳር  ጥቅምት25/2011 የአማራ ክልልን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ  እየተከናወኑ  ያሉት ተግባራት ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ። በክልሉ ሰላምና ደህንነት፣ በጣና ኃይቅ በተከሰተው የዕምቦጭ አረምና በላሊበላ ውቅር ዐብያተ ክርስቲያናት ላይ ያተኮረ ማብራሪያ ለምክር ቤቱ አባላት ሰጥተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት መንግሥትና የፀጥታ አስከባሪ አካላት ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት እያደረጉት ያሉት እንቅስቃሴ ውጤት እየተገኘበት ነው። እንደ አገር የተገኘው ለውጥ እንዳይቀለበስ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል። በአንዳንድ ቦታዎች መንገዶችን በመዝጋት ዜጎች ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ ለማድረግ የሚታየው አዝማሚያ በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል ብለዋል። የክልሉ መንግስት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን መፈናቀል ለማስቀረት ከሚመለከታቸው ጋር እየተወያየ  መሆኑን አቶ ገዱ ጠቁመዋል። የክልሉ አመራር ለተፈናቃዮች ጊዜያዊ ድጋፍ በማድረግ ወደነበሩበት ቀዬ ፈጥነው እንዲመለሱና ሌሎችም እንዳይፈናቀሉ ከአጎራባች ክልል አመራሮች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል። ከማንነት ጋር ተያይዞ ዜጎች ሰላማዊ በሆነ መልኩ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ህጋዊና ስርዓትን ተከትለው እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት  ስምምነት መደረሱን አስታውቀዋል። የጣና ኃይቅን ከተጋረጠበት የእምቦጭ አረም ለመከላከልም ባለፈው ሳምንት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ኃይቁን መመልከታቸውን ያስታወሱት አቶ ገዱ፣አረሙን ለማስወገድም የፌዴራል መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል ብለዋል። አሁን ያሉትን ማሽኖችና የሰው ኃይል በመጠቀም አረሙን በዘመቻ ለማስወገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል። እንዲሁም በላሊበላ ውቅር ዓብያተ ክርስቲያናት ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመከላከልና ቅርሱን ለመጠበቅ ክልሉ ከፌዴራል መንግስትና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር በጋራ ለመስራት መወሰኑን አስረድተዋል። ቅርሱን በዘላቂነት ከሚደርስበት ጥቃት ለመታደግም የተተከለውን መጠለያ በቀጣይ በማንሳት ጥገናው እንደሚከናወን ገልጸዋል። የምክር ቤቱ አባላት ወደየአካባቢያቸው ሲመለሱ ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥና ለህግ የበላይነት መከበር ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል። የክልሉ ሕዝብም ለውጡን ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን ሆኖ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ዘላቂነቱን እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም