ፕሪሚየር ሊጉን አዲስ የተቀላቀሉት ክለቦች በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሪሚየር ሊጉን አዲስ የተቀላቀሉት ክለቦች በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ
አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2011 ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀሉት ክለቦች በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ። ፕሪሚየር ሊጉን አዲስ የተቀላቀሉት ባህር ዳር ከተማ፣ ሽሬ እንዳ ስላሴና ደቡብ ፖሊስ በመጀመሪያው ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ያለፈው የከፍተኛ ሊግ ውድድሩ ወደ 2011 ዓ.ም በመራዘሙ ምክንያት "በቂ ዝግጅት ባለማድረጋችን ጨዋታው ይራዘምልን" የሚል ጥያቄ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቅርበው ነበር።ክለቦቹ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ጨዋታቸውን በዚህኛው ሳምንት እንዲጀምሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መወሰኑ የሚታወስ ነው። በዚሁ መሰረት የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብራቸውን ዛሬ ያካሂዳሉ። በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት በጳውሎስ ጌታቸው(ማንጎ) የሚሰለጥነው ባህር ዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል። ባህር ዳር ከተማ በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በምድብ ሀ አንደኛ በመውጣት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተቀላቀለ የመጀመሪያ ክለብ እንደሆነ ይታወሳል። አዲስ አዳጊው ቡድን ከ14 ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የመጀመሪያ ነጥቡን ለማስመዝገብ ከፍተኛ ፈተና ይጠብቀዋል። በአንጻሩ የፕሪሚየር ሊጉ ባለ ክብረ ወሰን አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሳምንት በፊት ፓርቹጋላዊውን አሰልጣኝ ማኑኤል ቫዝ ፒንቶን ያሰናበተው ክለቡ ያለ ዋና አሰልጣኝ ወደ ሜዳ ይገባል። ጅማ አባ ጅፋርን ተከትለው ባለፈው ዓመት በሊጉ ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ፈረሰኞቹ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ዳግም ለመጨበጥ የሚያደርጉትን ጉዞ ዛሬ ይጀምራሉ። በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው(ሞሪኒዮ) የሚመራው ደቡብ ፖሊስ በሀዋሳ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ደቡብ ፖሊስ በዘንድሮው ዓመት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈውን መከላከያን ያስተናግዳል። ደቡብ ፖሊስ ወደ ሊጉ ማደጉን ተከትሎ በዝውውር መስኮቱ በስፋት ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን አንጋፋውን የመሐል አማካይ ተጫዋች ሙሉዓለም ረጋሳን ማስፈረሙም ይታወቃል። አዲስ አዳጊው ቡድን በስዩም ከበደ የሚመራውን መከላከያን በመግጠም የመጀመሪያ ነጥቡን ለማስመዝገብ ይጫወታል። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫና የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባለቤት መከላከያ በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኝ ሲሆን የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ ከደቡብ ፖሊስ ጋር ይፋለማል። በሽሬ ስታዲየም ሌላኛው አዲስ የሊጉ ክለብ ስሑል ሽሬ(በቀድሞ መጠሪያቸው ሽሬ እንዳስላሴ) ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ከወላይታ ድቻ ጋር ይጫወታሉ። ጅማ አባ ቡናን አሸንፈው ሦስተኛ ቡድን በመሆን ወደ ሊጉ የመጡት ስሑል ሽሬዎች በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታቸው የመጀመሪያ ነጥባቸውን ለማግኘት ይጫወታሉ። በሊግ ውድድር ላይ አዳጊ ክለቦች የሚያደርጉትን ጨዋታ ማሸነፍ፣ መሸነፍና ነጥብ ይዞ መውጣት ቀጣይ ለሚኖራቸው ጨዋታዎች ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳላቸው የስፖርቱ ባለሙያዎች ሲገልጹ ይሰማል። ከአዲስ አዳጊዎቹ ክለቦች የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር በተጨማሪ የሁለተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። መቀመጫውንና ውክልናውን ወደ ትግራይ ያዞረው ደደቢት በመቀሌ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናግዳል። ደደቢት በመጀመሪያ ጨዋታው በመቐለ ሰብኣ እንደርታ (በቀድሞው መጠሪያ መቐለ ከተማ) የተሸነፈ ሲሆን በአንጻሩ ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል። በጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ፋሲል ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ይጫወታል። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ፋሲል ከተማ በመጀመሪያ ጨዋታው በሲዳማ ቡና የተሸነፈ ሲሆን በአንጻሩ በዘርዓይ ሙሉ የሚሰለጥነው ሀዋሳ ከተማ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን ማሸነፉ ይታወሳል። ትናንት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት በመቐለ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ መቐለ ሰብኣ እንደርታ በሳሙኤል ሳሊሶና አምበሉ ሚካኤል ደስታ ከማዕዘን ምት በቀጥታ ባስቆጠራት ግብ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። በገብረ መድህን ሃይሌ የሚሰለጥነው መቐለ ሰብኣ እንደርታ የመጀመሪያ ጨዋታውንም ደደቢትን አሸንፎ ስድስት ነጥብ በመሰብሰብ ፕሪሚየር ሊጉን መምራት የጀመረ ሲሆን በሊጉ ጠንካራ ጅማሬ አድርጓል። በአንጻሩ በሊጉ ሁለቱ ጨዋታዎችን የተሸነፈው የአስልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ በፕሪሚየር ሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።