ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር የሙከራ ጣቢያዋን ለመዝጋት እየሰራች መሆኑን የተለያዩ ሀገራት ጋዜጠኞች በአካል ተገኝተው እንዲዘግቡ ጋበዘች

54
ግንቦት 15/2010 ሰሜን ኮሪያ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች የኒዩክሌር ጣቢያውን እያፈራረሰች መሆኑን በአካል ተገኝተው እንዲዘግቡ ጋበዘች ፡፡ ሰሜን ኮሪያ በኒዩክሌር ማብለያ ጣቢያዋ ተገኝተው ጉብኝት እንዲያደርጉ የተላኩላትን የደቡብ ኮሪያ ጋዜጠኞች ዝርዝርም ተቀብላለች። ሁለቱ ሀገራት በአሜሪካና በደቡብ ኮሪያ የአየር ሃይል ወታደራዊ ልምምድ ምክንያት የቃላት ጦርነት ላይ መሰንበታቸው ይታወሳል። የደቡብ ኮሪያ የውህደት ሚኒስቴር  እንደገለፀው ሰሜን ኮሪያ በሀገሪቱ ተገኝተው የኒዩክሌር ማብለያ ጣቢያዋን ለመዝጋት እየሰራች መሆን አለመሆኑን እንዲዘግቡ የሩሲያ፣ የቻይና፣ የአሜሪካ፣ የዩናይይትድ ኪንግደም እና የደቡብ ኮሪያ ጋዜጠኞችን ጋብዛለች። በዚህም መሰረት ጋዜጠኞቹ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በኒዩክሌር ጣቢያው ተገኝተው ፒዮንግያንግ በተጨባጭ ያለችውን እየፈፀመች ነው ወይ የሚለውን ይዘግባሉ ተብሏል። በፑንግዬ-ሪ የሚገኘው የኒዩክሌር የሙከራ ጣቢያን ስራ ለማስቆም የማፍረስ ስራ እየሰራች መሆን አለመሆኑንም በአካል እነደሚጎበኙ ይጠበቃል። ሀገሪቱ ጋዜጠኞች በአካል ተገኝተው ተጨባጭ ስራውን እንዲመለከቱ መጋበዟ የኒዩክሌር ማብለያ ስራዋን ለማቆም ባልተጠበቀ መልኩ እየሄደች መሆኑን ያሳያል ነው የተባለው። ይህ የሰሜን ኮሪያ እርምጃም በኮሪያ ልሳነ ምድር ለዓመታት በውጥረት የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማርገብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ይጠበቃል። ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ጋዜጠኞች በሰሜን ኮሪያ የወደብ ከተማ ዎንሳን ትናንት ማምሻውን የገቡ ሲሆን ከዛሬ እስከ አርብ ለሚያደርጉት የኒዩክሌር ሙከራ ጣቢያ ጉብኝት ማብራሪያ ይሰጣቸዋል። የደቡብ ኮሪያ ጋዜጠኞች በቤጂንግ በኩል የፒዮንግያንግ ቪዛ ባለማግኘታቸው ወደ ሀገራቸው ቢመለሱም በዛሬው እለት ሰሜን ኮሪያ ስምንት ደቡብ ኮሪያውያን ጋዜጠኞችን እንደምትቀበል አስታውቃለች። የደቡብ ኮሪያ የውህደት ሚኒስቴር ፒዮንግያንግ ስምንት ጋዜጠኞችን ለመቀበል ውሳኔ ማሳለፏን አድንቋል። ጋዜጠኞቹም በዛሬው እለት በመንግስት አውሮፕላን ከሴኡል የአየር ሃይል ምድብ ተነስተው በቀጥታ ወደ ዎንሳን ከተማ በረራ እንደሚያደርጉ እየተጠበቀ ነው። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ባይክ ታኤ ሃዩን ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር መርሃ ግብሯን ሙሉ በሙሉ ለማቆም እየሰራች መሆኗን በትክክለኛ ሁኔታ እንድንገነዘብ የጋዜጠኞቹ መጋበዝ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።

ምንጭ፦ሲ ጂ ቲ ኤን እና ሬውተርስ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም