የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ተመሰረተ
አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2011 የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ዛሬ ተመሰረተ። በአገሪቱ በሚገኙ 31 ማህበራት የተመሰረተው ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፉን ምጣኔ ኃብታዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት የማገዝ ዓላማ አለው። ፌዴሬሽኑን የመሰረቱት የፈሳሽና ደረቅ ጭነት፣ የህዝብ ማመላለሻ፣ ታክሲ እንዲሁም ሌሎች በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራት ናቸው። ፌዴሬሽኑን ለመፍጠር ባለፉት 17 አመታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፤ ሆኖም ባለፉት ሶስት ዓመታት በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ ነው ዛሬ እውን ሊሆን የቻለው ተብሏል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘርዑ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከዘርፉ ጋር በተያያዘ የሚታዩትን የተለያዩ ፈተናዎች በመቋቋም መፍትሄ ለመዘየድ እና የዘርፉን ልማት ለማፋጠን የፌዴሬሽኑ ምስረታ ወሳኝ ነው። "እንደ ንብ ያለእረፍት ካልሰራን የልማቱን ማር ማምረትና መመገብ አንችልምና ፌዴሬሽኑን በጋራ እውቀትና ጉልበት በማጠንከር በመንግስት የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል መደመር ይገባናል" ሲሉም ገልጸዋል። "በአንድነት መሰባሰባችን ግዴታችንን ለመወጣትና መብታችንን ለማስከበር እንዲሁም ጥቅማችንን ለማስጠበቅ አስተዋፅኦው የጎላ ነውም" ብለዋል። በማህበር መደራጀት በመንግስት የተነደፉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ለማድረግ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ፍቃዱ ገብሩ ናቸው። ፌዴሬሽኑ የአባላቱን መብትና ጥቅም ከማስከበር ባሻገር የአገር ጥቅምን ያስጠብቃል ብለን እናምናለን ያሉት አቶ ፍቃዱ በቀጣይም አሰሪና ሰራተኛን የተመለከቱ ህጎችን ማመንጨትና መተግበር ላይ ጉልህ ሚና ይወጣል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ የአባላቱን ቁጥርና አቅም ለማሳደግ መስራት አለበት ያሉት ተወካዩ መንግስት ፌዴሬሽኑ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፍም ቃል ገብተዋል። የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው የፌዴሬሽኑ ምስረታ የትራንስፖርት ሎጅስቲክ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም ዘርፉን ለማዘመን ትልቅ ተስፋ እንዳለው ጠቅሰዋል። ወይዘሮ ሙሉ እንዳሉት ዘርፉ ለአገሪቱ ምጣኔ ኃብት አድገት ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የዘርፉን ስኬት ለማረጋገጥ በከፍተኛ ትጋት በመስራት ለላቀ ውጤታማነት ሊሰራ ይገባል። የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን የትራንስፖርት ማህበራት፣ ድርጅቶችና ተቋማትን አባል በማድረግ ዘርፉ ለምጣኔ ኃብት እድገት የሚጠበቅበትን ሚና እዲጫወት ይደረጋል ተብሏል።