ቀጥታ፡

የፍትህ ሥርዓቱን ለማሻሻል የተጀመረው ጥረት ወቅታዊ ጥያቄዎችን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት ተባለ

አዲ አበባ ጥቅምት 24/2011 በኢትዮጵያ የፍትህ ሥርዓቱን ለማሻሻል የተጀመረው እንቅስቃሴ ወቅታዊ፣ የህዝብ ጥያቄዎችን መሰረት ያደረገ እና ሁሉን አቀፍ እንዲሆን የመስኩ ምሁራን ጠየቁ። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የሕግ ማሻሻያ ሥራዎቹ የሚከናወኑት የሕዝቡን የፍትህ ፍላጎት ማርካት በሚያስችል መንገድ ነው ይላል። መንግስት ቅሬታ እየቀረበባቸው ያሉትን አዋጆችና ህጎችን በማካተት አጠቃላይ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል እንዲቻል የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ምክር ቤት አቋቁሞ ወደ ስራ ከገባ ጥቂት ወራት ተቆጥረዋል። በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት የፀረ-ሽብር እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጆችን ጨምሮ ሌሎች ህጎችን ለማሻሻል የሚያስችሉ ጥናቶችና ውይይቶች በመካሄድ ላይ ናቸው። ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን፤ ይህ ህግ የማሻሻል ተግባር፤ ሁሉን አቀፍና ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል ነው የሚሉት። ምሁራኑ እንደተናገሩት የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያ ተግባሩ ከሕገ-መንግስት ጀምሮ በተዋረድ እስከታችኛው እርከን ያሉ ሕጎችን በቅጡ ማጤን ይጠበቅበታል። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ  ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ መሐመድ ሱዋህን "የፍትህ ሥርዓቱ ማሻሻያዎች አገራዊ ይዘት መላበስ አለባቸው" ይላሉ። በሕጎቹ ያሉትን ክፍተቶች በጥልቀት በመመርመር በአግባቡ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባም ነው የጠቆሙት። በዩኒቨርሲቲው የሕግና ፌደራሊዝም ትምህርት ቤት ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ አባተ በበኩላቸው በተለይም ለእድገት ማነቆ የሆኑና ለአገራዊ የልማት እንቅስቃሴ እንቅፋት የሆኑ ሕጎችን መፈተሽና ማስተካከል እንደሚገባ አስረድተዋል።  የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ የኮሚኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከጀመረው አጠቃላይ የለውጥ እርምጃ ውስጥ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያው ነው። ሥራዎቹም የሰፊውን ሕብረተሰብ የፍትህ ፍላጎት እርካታ ለማጠናከር እና በተቋማቱ ላይም የዜጎችን አመኔታ ለማጎልበት በሚያስችል መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ የሪፎርም ስራ የዜጎች መብት የበላይነት እንዲረጋገጥ  ከማስቻል ባለፈ ፍትህ የሰፈነባትና ዲሞክራሲያዊ አገር ለመፍጠር የሚያስችል ነው ሲሉም  አቶ ዝናቡ ቱኑ ተናግረዋል።     ዳይሬክተሩ አክለውም ባለፈው ሩብ ዓመት በተከናወኑ አንዳንድ የሪፎርም ተግባራት ለውጥ እየታየ መሆኑን ጠቁመው ከዚህ አኳያ በማረሚያ ቤቶች አካባቢ ያለውን የታራሚዎች አያያዝ ስርዓት ለማስያዘ የተወሰደው እርምጃ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም