የአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉን ጠቅላይ አቃቢ ህግ መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ አፀደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉን ጠቅላይ አቃቢ ህግ መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ አፀደቀ
ባህርዳር ጥቅምት 24/2011 የአማራ ክልል ምክር ቤት በ11ኛ መደበኛ ጉባኤው የክልሉን ጠቅላይ አቃቢ ህግ መስሪያ ቤት ለሟቋቋምና ስልጣንና ተግባሩን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ በመመርመር ዛሬ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ። አዋጁን ማውጣት ያስፈለገውም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን ሰብአዊና ዴሜክራሲያዊ መብቶች ለማክበርና በተበታተነ መልኩ በተለያዩ ተቋማት ሲሰጡ የቆዩ አሰራሮችን ወደ አንድ ለማሰባሰብ ነው ተብሏል። የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍርዴ ቸሩ እንደገለጹት ቀደም ሲል የአቃቤ ህግነት ስራ በፍትህ ቢሮ፣ በክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በንግድ ቢሮና በገቢዎች ባለስልጣን ተቋማት በተበታተነ መልኩ ሲሰጥ ቆይቷል። ከስራው ውስብስብነት አንፃር በገቢዎች ባለስልጣን በኩል የሚሰራው የአቃቤ ህግ ተግባር ለጊዜው ባለበት ተቋም እንዲቀጥል በአዋጁ መቀመጡን ተናግረዋል። የሚያከናውናቸውን የህግ ስራዎች አዲስ ለተቋቋመው ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት በየጊዜው በሪፖርት እንዲያሳውቅ አዋጁ እንደሚያስገድድም አቶ ፍርዴ አስረድተዋል። የንግድና የፀረ-ሙስና የክስ ጉዳይን የሚከታተሉት አቃብያነ ህጎች ደግሞ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ጋር እንዲሰባሰቡ መደረጉን ተናግረዋል። ለክልሉ አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ተሰጥቶ የቆየው የሰነዶች ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ኃላፊነት አዲስ ወደ ተቋቋመው ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት እንዲካተት መደረጉን ጠቁመዋል። በተቋማት የምርመራ ስራ ሲያከናውኑ የቆዩ አካላት ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሰጡ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ አዲሱ አደረጃጀት ጠንካራ ህግን የሚያስከብር ተቋም ለመፍጠር እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ሰጤ ናቸው። የወንጀልና የፍትሃብሔር ጉዳዮች በክልሉ በተቋቋመው ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት እንዲሰባሰቡ መደረጉም ከፌዴራል ጋር የሚደረገውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር የህግ አማካሪ አቶ መርሃ ፅድቅ መኮንን በሰጡት ማብራሪያ በተበታተነ አደረጃጀት ውጤታማ የህግ ማስከበር ስራ ማከናወን ስለማይቻል የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ማቀቋሚያ አዋጅን ማውጣት አስፈልጓል። “አዲሱ መስሪያ ቤት የክልሉ መንግስት የሚያከናውናቸው ስራዎች በህግ አግባብ መመራታቸውን የሚከታተልና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያስችል ነው” ያሉት አማካሪው ተቋሙ በተሟላ ነጻነት እንዲሰራ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል። የክልሉን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለማቋቋምና ስልጣንና ተግባሩን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ የምክር ቤቱ ከተወያየ በኋላ የሚካተቱ ነጥቦች እንዲጨመሩ በማድረግ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።