ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አሰሪዎች የጋራ የምክክር መድረክ ሊመሰረት ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2011 የኢትዮጵያ አሰሪዎች የጋራ የምክክር መድረክ በሶስት ወር ውስጥ ሊመሰረት መሆኑን የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ገለፀ። መድረኩ በተለይ በዘርፍ ያልተደራጁ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል። የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን ለኢዜአ እንደተናገሩት መድረኩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የሚሳተፉበት ሲሆን በየሶስት ወሩ የሚካሄድ ነው። በመድረኩ በአሰሪዎች በሚገጥማቸው ችግሮች፣ ባሏቸው ጥንካሬዎችና ጉድለቶች ላይ ውይይት የሚያደርግ እንደሚሆንም ተናግረዋል። ለአገሪቱ ልማት ጉልበቱን፣ ገንዘቡን፣ ጊዜውን የሚያውል እንዲሁም የሰለጠነ አገር ወዳድ አሰሪ እንዲኖር ምክክር የሚደረግበትም ነው ብለዋል። የማያሰሩ ፖሊሲዎችና ሁኔታዎች ሲፈጠሩ እየተመካከሩ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦች የሚቀርቡበት እንደሚሆንም ነው የገለፁት። የውጭ ባለሃብቶችና የአገር ውስጥ አሰሪዎችም ከመንግስት ጋር በመገናኘት ምክክርና ውይይት የሚያደርጉበት ይህ መድረክ አሰሪዎች እርስ በእርስ የሚማማሩበትና ልምድ የሚለዋወጡበት እንደሆነም አስረድተዋል። መድረኩ የቴክኖሎጂ ሽግግርና በተለይም በአገር ውስጥ ምርቶች ላይ የተመረኮዘ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር ለማድረግ አሰሪዎች አንዱ ከሌላው ግብዓት እንዲወስዱ ለማድረግ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት። መድረኩ መተዋወቂያ ከመሆን ባሻገር ሲምፖዚየሞችና ኤግዚቢሽኖችን በማደራጀት በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ አሰራሮች የሚፈጠሩበት እንደሚሆንም ይጠበቃል። አሰሪና ሰራተኛ ከመንግስት ጋር ተባብረው እንዲሰሩ፣ መንግስት የሚያሰሩ ህግና ደንቦችን እንዲያዘጋጅና በሶስትዮሽ ተቀራርበው ለመስራት የሚያስችል አደረጃጀት ነውም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ። በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ይመሰረታል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ መድረክ የቱርክ፣ የቻይና፣ የህንድ፣ የኢጣልያ እና የአሜሪካ ባለሃብቶች እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፍ ያልታቀፉ ባለሃብቶች ድምፃቸው ይሰማል ተብሏል። አዳዲስ መመሪያዎችና ደንቦች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠርና ምቹ የስራ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስችል በስርዓት የሚመራ የአሰሪ አደረጃጀት እንዲኖርም ያግዛል። የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን በፌዴሬሽኖች የተመሰረተ ሲሆን በመንግስት የአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድና የአማካሪ ቦርድነት የሚሳተፍ አደረጃጀት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም