በአዲስ አበባና ዙሪያዋ አራት የአትሌቲክስ የመለማመጃ ቦታዎች ይዘጋጃሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባና ዙሪያዋ አራት የአትሌቲክስ የመለማመጃ ቦታዎች ይዘጋጃሉ
አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2011 በአዲስ አበባና ዙሪያዋ አራት የአትሌቲክስ የመለማመጃ ቦታዎች ለማዘጋጀት መታቀዱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ። ፌዴሬሽኑ 22ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል። የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ እንደገለጹት በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የሚታዩ የአትሌቶች የመለማመጃ ቦታዎችን እጥረት ለማቃለል ታቅዷል። የእነዚህ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታም ከለገጣፎ ከተማ አስተዳደር ጋር ተነጋግሮ በጎ ምላሽ ማግኘቱንም ገልጸዋል። ቀሪዎቹ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ደግሞ በሰንዳፋና ቃሊቲ ለመስራት እንደታሰበ ነው የገለጹት። ከዚህ በተጨማሪ በ2011 ዓ.ም ፌዴሬሽኑ የገንዘብ ምንጩን ለማጠናከር 137 ሱቆችን በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ዙሪያ ለመስራት አቅዷል። ፌዴሬሽኑ በጠቅላላ ጉባኤው ለክለቦችና ከተማ አስተዳደሮች የዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት እንደሚሰጥ ይጠበቃል።