ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን በመካከለኛው ምስራቅ ተዘዋውረው መስራት የሚችሉበት ጥናት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2011 በተለያየ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ ኢትዮጵያውያን በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ተዘዋውረው መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮጵያ መንግስት በሳዑዲ አረቢያ፣ በኳታርና በዮርዳኖስ በቤት ውስጥ ሰራተኝነት ለሚሰማሩ ዜጎች ከአገሮቹ ጋር ህጋዊ የስራ ስምሪት ስምምነት ማድረጉ ይታወቃል። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ይርጋለም ለኢዜአ እንደገለጹት በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የሚሰማሩ ዜጎች የስራ ስምሪታቸውን በተመለከተ የሌሎች አገሮችን ልምድ መነሻ በማድረግ ጥናት እየተካሄደ ነው። የስራ ስምሪቱን ህጋዊ ለማድረግ በሚካሄደው ጥናት የፖሊሲና ህግ ማሻሻያ ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በነርሲንግ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በአሽከርካሪነትና በመካኒክነት ሙያዎች የሰለጠኑ ዜጎች ወደተለያዩ አገሮች በማቅናት በሙያቸው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ በህገ-ወጥ መንገድ ወደተለያዩ አገሮች ለስራ በሚሄዱ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሰብዓዊና አካላዊ ጉዳት ለመቀነስ የስራ ስምምነት ከተደረገባቸው በተጨማሪ በሌሎችም የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ህጋዊ የስራ ስምሪት ለማድረግ በጥናት የታገዘ ስራ እየሰራ መሆኑን አቶ አሰፋ አብራርተዋል። በአገሪቱ የሰው ኃይል እጥረት የሌለባቸውን የሙያ መስኮች በመለየት የተቀባይ አገሮችን የሙያ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ዜጎችን ለማሰማራት ጥናት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል። በሚኒስቴሩ የሚካሄደው ጥናት በአገሪቱ ያለውን የስራ አጥ ቁጥር ከመቀነስ ባሻገር ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቀነስ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አቶ አሰፋ አስረድተዋል። ሚኒስቴሩ የሚያካሂደውን ጥናት ፈጥኖ በማጠናቀቅ የስራ ስምሪቱን ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ያሉት ዳይሬክተሩ ዜጎች ወደተለያዩ አገሮች ተዘዋውረው ለመስራት ሲሞክሩ ህጋዊ የጉዞ አካሄድን ብቻ መከተል እንዳለባቸው አሳስበዋል። ዜጎች መንግስት በአገር ውስጥ የሚያመቻቸውን የስራ ዕድል እና የስራ ፈጣሪነት አመለካከት የመጀመሪያ አማራጫቸው እንዲሆን አቶ አሰፋ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም