አጓጊ የቢዝነስ አማራጮችና ተተግባሪ ትልሞች ያሏት ሃገር

31
ኢዜአ ሞኒተሪንግ “ኢትዮዽያ- የቃል ኪዳኗ ምድር” በሚል ርዕስ ጸሁፉን የጀመረው  ቢዝነስ ትራቭለር ሃገሪቷ ያላትን ወጣት ሀይል በመጠቀምና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመለወጥ ትኩረት ያደረጉባቸውን ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ትልሞችን በመመርኮዝ ወደ ስኬት እንደምትንደረደር ተስፋ ያጫረ ሃሳቡን አስፍሯል። ኢትዮዽያ ከሌሎች ሃገራት የሚለዩዋት በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ የሚያነሳው ፅሁፉ ሃገሪቷ ያላትን የራሷን የቀን መቁጠሪያ ለአብነት ያነሳል። የቀን መቁጠሪያው ከሌሎች የዘመን አቆጣጠር ወደ ኋላ ሰባት/ስምንት አመታትን ይመልሰናል፤ የሰኣት አቆጣጠሯም ቢሆን እንደ ሌሎቹ 24 ሰኣታትን በሙሉ ሲቆጥር የሚውል ሳይሆን ቀኑን በ12 ሰአታት ምሽቱን ደግሞ በሌላ 12 ሰአታት በመክፈል ቀለል ያለ የሰኣት አቆጣጠርን ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ በወጉ መሰደሩን ፅሁፉ አስረድቷል። እንደ ቢዝነስ ትራቭለር ሞቅ ደመቅ ያለችው አዲስ አበባ በየትኛውም አካባቢ ለሚኖር የሃገሬው ዜጋ ሙቀቷን ታጋራለች። አላስፈላጊ መጫጫኖች ለሚሰማው ሁሉ ከተማዋ ፈውስን ታድለዋለች። አዲሱም ጊዜ ያለፈበትም በአንድ ላይ የሚገኝባት ሃገርም ናት፤ ኢትዮዽያ። በቀደመው የምስራቁ ክፍል ኖሮ ወደ ከተማዋ ለመጣ እንግዳ በሰማያዊ ቀለም ተመሳስሎ የሚታይባቸው ታክሲዎች ሃገሩ እንዳለ እንዲቆጥረው ያደርጉታል። በሌላ አማራጭም ቢጫ ቀለም ያላቸውን ታከሲዎች መጠቀምንም ከተማዋ ፈቅዳለች። የትኛውንም አይነት ታክሲ የሚጠቀም ሰው ግን ለዋጋ ክርክር ራሱን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። ከመቶ ሚሊዮን የሚልቀው የህዝብ ቁጥሯ ሃገሪቷን ለቢዝነስ አማራጭነት እንድትታጭ አድርጓታል። “ወጣቶች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በርካታ አማራጮች የተዘጋጁላቸው ቢሆንም የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ለተማሩ ወጣቶች በቂ የስራ አመራጭን ሊፈጥር አልቻለም። ይህ ነው ትልቁ ፈታኝ ሁኔታ። ለውጭ ባለሃብቶች ግን የተማረ የሰው ሃይልን በቀላሉ ለማግኘት ሰፊ ዕድል ተመቻችቶላቸዋል።” ሲሉ አንድ የኢትዮዽያ የአለም አቀፍ ንግድ ሃላፊ የተናገሩትን ቢዝነስ ትራቭለር በፅሁፉ አካቷል። ቢዝነስ ትራቭለር ፅሁፉን ሲቀጥልም ኢትዮዽያ የራሷ የሆነ የውስጥ ችግር ቢኖርባትም ከጎረቤቶቿ አንፃር ስትታይ ግን ሰላማዊት ሃገር እንደሆነች አስቀምጧል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እኤአ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እስከያዝነው ዘመን የዘለቀውን የኢትዮዽያና ኤርትራ የሰላም እጦት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በመነጋገር የሰላም ስምምነት እንዲኖር ትልቁን ሚና ወስደዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሃላፊነት በመጡ ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ታላቅ ምጣኔ ሃብታዊ ብስራትን አሰሙ። ሁለቱ ግዙፍ የመንግስት ተቋማትን ማለትም ቴሌን እና የኢትዮዽያ አየር መንገድን ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ክፍት አደረጉ። እኤአ በ2025 በአፍሪካ ተወዳዳሪ እና መሪ አየር መንገድ የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየተጓዘ ለሚገኘው ተቋም ሌላ የመጠናከሪያ ውሳኔ ሆነለት። አየር መንገዱ የአውሮፕላን ቁጥሩን ከ100 ወደ 140 የማሳደጉ ዕቅድ በራዕዩ ውስጥ የሚካተት ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ተቋሙ 120 አለም አቀፍ መዳረሻዎች እና 20 የሃገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎች አሉት፡፡ አየር መንገዱን የሚጠቀሙ ተጓⶶች ቁጥርም ባለፉት ሰባት አመታት ከነበረበት 3ሚሊዮን ወደ ስምንት ሚሊዮን አድጓል። የ153 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበውን የተቋሙ ገቢ በ2025 አስር ቢሊዮን ዶላር የማድረስ ዕቅድ አስቀምጧል። ከኢትዮዽያ ጋር ቢዝነስ ለመስራት የሚፈልግ ሃገሪቷ ሌሎች ገፀ በረከቶች አሏት የሚለው ቢዝነስ ትራቭለር ጋዝና ነዳጅ ዘይት ሌላው አማራጭ እንደሆነም ያነሳል። የነዳጅ ፍለጋው እየተካሄደባቸው የሚገኙት የሶማሌ ክልል፣ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ የሃገሪቱ አካባቢዎች ሃገሪቷ ያላትን ሰፊ ዕድል ጠቋሚዎች ናቸው። የማዕድን ልማት፣ የግብርና ማቀነባበሪያዎች እና ማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም የሌዘር እና ጨርቃጨርቅ ዘርፎች በስለው የተዘጋጁ የኢንቨስትመንት ዕምቅ አቅሞች ናቸው። መንግስት አስር የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙ ደግሞ ሌላው የማይገኝ አጋጣሚ ነው። ዩኑሊቨር፣ ዲያጂኦ እና ፒታርድስ የተሰኙት ከአውሮፓ የመጡ ኩባንያዎች በሃገር ውስጥ በተግባር ላይ መገኘታቸው ደግሞ ከላይ ለቀረበው መረጃ ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ፒታርድስ የተሰኘው ኩባንያ ጥሬ ቆዳን ከሃገር ውስጥ ገበያ በመግዛት የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን እያመረተ ለአለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል። ኩባንያው ካሉት አምስት ፋብሪካዎች አራቱ በመዲናዋ የሚገኙ ሲሆን አንዱ በሞጆ አቅራቢያ እንደሚገኝም ቢዝነስ ትራቭለር አመልክቷል። “1500 ሰራተኞች አሉን፤ ሁሉም ኢትዮዽያውያን ናቸው። ሃገሪቷ በርካታ ዕድሎችን ይዛለች። …የጊዜ ሂደቷም ከአውሮፓ ጋር ይቀራረባል፤ የተማረ የሰው ሃይል እና ልማትን የተጠማ ህዝብን ሃገሪቷ ይዛለች።” በማለት የፒታርድስ ኩባንያ ዋና ሃላፊ ሬግ ሃንኬይ ለመረጃው ምንጭ ተናግረዋል። የሃገሪቱ ምጣኔ ሃብት ዕድገት ሲያስመዘግብ የህዝቡ የመግዛት አቅም እያደገ መምጣቱን አሁን በሃገሪቱ ሄኒከን እና ዲያጂኦ በተሰኙት የቢራ ፋብሪካዎች የሚመረተውን ቢራ የሚጠቀም የማህበረሰብ ክፍል መጨመሩን በዋቢነት በማንሳት ፅሁፉ ያስረግጣል። በተለያዩ አካባቢዎች ቀልጣፋ የቢሮክራሲ አሰራሮችን በፍጥነት መተግበር ብሎም የመንገድ ፣ የመብራትና የባቡር መሰረተ ልማቶችን ማሳደግ አለፍ ሲልም ማዘመን እንዲሁም የሎጂስቲክ አተገባበሯን ማሻሻል ሃገሪቷ መልካም ዕድሎቿን በመጠቀም የህዝቧን ህይወት ለመቀየር አይነተኛ ሚናዎች ናቸው ሲል ቢዝነስ ትራቭለር ፅሁፉን ቋጭቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም