ምክር ቤቱ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ማሻሻል ላይ ውሳኔ አሳለፈ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ማሻሻል ላይ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2011 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 55ኛ መደበኛ ስብሰባ የመከላከያ ሰራዊት ማሻሻያ አዋጅን ጨምሮ በአራት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ። ውሳኔ ከተላለፈባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የአገር መከላከያ ሰራዊቱን የሚመለከት ሲሆን የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ቁጥር 809/2006ን ለማሻሻል የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል። በአገሪቷ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ መከላከያ ሰራዊቱ አገራዊ ተልዕኮውን በተሻለ ብቃት እንዲወጣ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሰው ምክር ቤቱ የሰራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸም ብቃት ለማጠናከርም የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊ መሆኑን አመልክቷል። በመሆኑም ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ማሻሻያዎችን በማከል ረቂቅ አዋጁ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኳል። ምክር ቤቱ በሌላ በኩል የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የተዘጋጀውን ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ደንቡ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል። ቀደም ሲል የስራ ዕድል ፈጠራ ስራዎች በተለያዩ መስሪያቤቶች ወጥነት በጎደለውና ያለበቂ ዝግጅት ሲከናወን ነበር። ይህን ችግር ለመፍታት የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መቋቋሙ ይታወሳል። የኮሚሽኑን ተግባርና ሃላፊነት የሚወሰነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ረቂቅ ደንቡን አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቧል። ምክር ቤቱ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት እንዲሁም የፌዴራል ዓቃቢያን ህግ መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ ተግባርና ሃላፊነትን ለመሰወን በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይም ተወያይቶ ደንቡ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል። የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩትና የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በቅርቡ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተብሎ መቋቋሙ ይታወሳል። የኢንስቲትዩቱን ስልጣን፣ ተግባርና አደረጃጀት ለመወሰን የፕላንና ልማት ኮሚሽን ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ባቀረበው መሰረት ነው ምክር ቤቱ ዛሬ ውሳኔ ያሳለፈው። በተመሳሳይ በስራ ላይ ያለው የፌዴራል ዓቃቢያን ህግ መተዳደሪያ ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ስራ ላይ ከዋለ ረጅም ዓመታት ያሳለፈ በመሆኑ በአሰራር የታዩ ክፍተቶችና ሎላዊነት ያስከተላቸው ለውጦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ደንቡን መለወጥ እንዳስፈለገ ተመልክቷል።