የወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ መሾም በፍትህ ስርዓቱ ችግሮችን ለመፍታት ሴቶች ሚና እንዳላቸው የሚያሳይ ነው---ሴት ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ መሾም በፍትህ ስርዓቱ ችግሮችን ለመፍታት ሴቶች ሚና እንዳላቸው የሚያሳይ ነው---ሴት ምሁራን
አርባምንጭ ጥቅምት 24/2011 ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የፈዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸው በፍትህ ተቋማት ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሴቶች ሚና እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴት ምሁራን ተናገሩ፡፡ የወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ሹመትን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ሴት ምሁራን መንግስት የፍትህ ስርዓቱን ከማሻሻል አኳያ ለሴቶች የሰጠው እውቅና እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ በዘርፉ በቂ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያላቸው ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸው በፍትህ ተቋማት ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንሚረዳ ነው ሴት ምሁራኑ የተናገሩት፡፡ በዩኒቨርስቲው የኢኮኖሚክስ መምህርት አምሳሌ ተክለ በሰጡት አስተያየት " እድል እንጂ ችሎታ ያላጡት ሴቶች የተሻለ ሥራ እየሰሩ በመሆናቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እውቅና ማግኘት ጀምረዋል "ብለዋል፡፡ በህግ ሙያ ካካበቱት ልምድ በተጨማሪ ለሴቶችና ህጻናት መብቶች ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት መይዘሮ መዓዛ ያላቸውን ልምድና የትምህርት ዝግጅት ተጠቅመው በፍትህ ስርዓቱ የሚታየውን ክፍተት መሙላት እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ሴቶች በተፈጥሮአዊ ባህሪይ የሚሰጣቸውን ኃላፊነት በታማኝነት የመወጣት ጸጋ እንዳላቸው የተናገሩት መምህርቷ በትልልቅ አገራዊ ኃላፊነቶች የተጀመረው የሴቶች ተሳትፎ በፌዴራል ደረጃ ብቻ ሳይወሰን እስከ ቀበሌ ባሉ መዋቅሮች መውረድ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡ ወይዘሮ መዓዛ ካላቸው የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ በላይ የተግባር ሰው በመሆናቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የህክምና ሳይንስ መምህርት ህይወት ታደሰ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ፍትህ በእጅጉ በመዛባቱ ይበልጥ ሴቶችን ተጠቂ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት መምህርት ህይወት በፍትህ ስርዓቱ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ የተሻለ አሰራር ሊያመጡ እንደሚችሉ እምነቴ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ "ፍርድ ቤቶች በፖለቲካ ጫና ውስጥ መውደቃቸው ለፍትህ መዛባቱ ምክንያት ነው" ያሉት መምህርት ህይወት የእሳቸው መመረጥ የፍትህ ተቋማትን ነፃነት ከማስጠበቅም በላይ በፍትህ ተቋማት ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቀነስ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ የአማርኛ ቋንቋ መምህርት አለምነሽ የኔነህ በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተፈጠረውን የለውጥ ሂደት ተከትሎ በውሳኔ ሰጭነት የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል ፡፡ አስተያየት ሰጪዋ እንዳመለከቱት በትላልቅ የኃላፊነት ቦታዎች የሴቶች ተሳትፎ ማደጉ ሌሎች ሴቶች ጠንክረው እንዲሰሩ ያግዛቸዋል፤ አዲሷ ተሿሚ አመኔታ ያጣው የአገሪቱ የፍትህ ስርዓት በችግሩ ተጎጂ የሆኑ ሴቶችና ህፃናትን እንዲታደግ መስራት አለባቸው፡፡ በፈዴራል ደረጃ ለሴቶች ችሎታ እውቅና መሰጠቱ እንደሚያደንቁ የተናገሩት መምህርት አለምነሽ "በተዋረድ ባሉ መዋቅሮች የሚታየውን የአመለካከት ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል ፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አድርጎ መሾሙ የሚታወስ ነው፡፡