በመዲናዋ የንፅህና ችግር ባለባቸው የምግብና መጠጥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

103
ግንቦት 15/2010 በአዲስ አበባ ንጽህናውን ያልጠበቀ መጸዳጃ ቤት ፣ ምግብ ማብሰያና ለተጠቃሚው ደረጃውን ያልጠበቀ አገልግሎት የሚሰጡ  ተቋማት ተጠያቂ አለመሆናቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በበኩሉ ደረጃቸውን  ያልጠበቁ  ምግብና መጠጥ  ቤቶች ላይ አስከ ማሸግ የሚደርስ እርምጃ  እየወሰድኩ ነው ብሏል። የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ሃብታሙ መንግስቱ  በመዲናዋ  አንዳንድ አካባቢዎች ያሉ  ምግብ ቤቶች የማብሰያና  የመጸዳጃ  ቤት የንጽህና ጉድለት የሚታይባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መጸዳጃ ቤቶቹ  ከምግብ ማብሰያው ጋር የተያያዙና ለምግብ ቤት ቅርብ በመሆናቸው  ምግብ ለመመገብም ሆነ ለመዝናናት አመቺ አለመሆናቸውንም አንስተዋል፡፡ የንጽህና ጉድለት ያለበትን ምግብ ተመግበው በመታመማቸው በህክምና እርዳታ መዳናቸውን  የገለፁት ደግሞ አቶ አብርሃም ሚካኤል ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው ሆቴሎች የምግብ አብሳዮች የሥራ ልብስም ቆሽሾ እንደሚታይ ነው የገለጹት፡፡ በከተማዋ በአንዳንድ  መጠጥ መሸጫ  ቤቶችም የመጸዳጃ አገልግሎት  ንጽህናውን ያልጠበቀ ከመሆኑ በተጨማሪ  የውሀ አገልግሎት የሌለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ችግሩን እየፈጠሩ በሚገኙ የምግብና የመጠጥ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ ክትትልና እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ  ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወ/ሪት ራሄል ተሾመ እንዳለችው  አንዳንድ ኬክ ቤቶችና ሆቴሎች መፀዳጃ ቤት የመቆለፍ ፣የለም የማለት ሁኔታ ይስተዋላል። ችግሩን እየፈጠሩ በሚገኙ ተቋማት ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ   ነው የገለጸችው፡፡ አራት ኪሎ  አካባቢ  በምግብና መጠጥ ቤት የሚሰሩት  አቶ አሸናፊ ባሀሩ በሰጡት አስተያየት አንዳንድ ተጠቃሚዎች በሃላፊነት ስሜት ባለመጠቀማቸውና በቦታ  ጥበት  ምክንያት የመጸዳጃ ቤቱ ሽታ ወደ ምግብና መጠጥ ቤቱ እንዲገባ አድርጓል ይላሉ። ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ሽታ ማጥፊያ እንደሚጠቀሙ የገለፁት አቶ አሸናፊ ውሀ በማይኖርበት ጊዜ መጸዳጃ ቤቱን ለመዝጋት እንገደዳለን ብለዋል። ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው በፒያሳ አካባቢ የሆቴል ሥራ አስኪያጅ በቤቱ ጥበት ምክንያት ምግብና መጠጥ መሸጫው፣ የምግብ ማብሰያውና መጸዳጃ ቤቱ ብዙም የተራራቁ አለመሆኑን ተናግሯል፡፡ መጸዳጃ ቤቱ ንጹህ እንዲሆንና መጥፎ ሽታ እንዳያመጣ ሎሚና የተለያዩ ሽታ ማጥፊያ ከመጠቀማቸው በተጨማሪ  በተደጋጋሚ  እንዲፀዳ  ይደረጋልም ነው ያለው። የአዲስ አበባ መድሃኒት እንክብካቤና ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ መጠጥ ጤና ነክ  ኢንዱስትሪ ቁጥጥር የስራ ሂደት ተወካይ አቶ አባዲ አብርሃ ችግሩ በከተማው በስፋት መታየቱን  ጠቅሰዋል። ባለሥልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ4ሺህ 826  የምግብና የመጠጥ አገልግሎት አቅራቢዎች  ላይ እርምጃ  መውሰዱን ገልጸው ከነዚህም ውስጥ 196ቱ ሲታሸጉ ቀሪዎቹ በቃልና በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ  ታልፈዋል ብለዋል። እየተሰራበት ያለው መመሪያ  ክፍተት ያለበት በመሆኑ ችግር ያለባቸው አገልግሎት ሰጪዎች ላይ  በተፈለገው ደረጃ  እርምጃ ለመውሰድ ባለማስቻሉ መመሪያውን እየተከለሰ መሆኑን  አቶ አባዲ ተናግረዋል። ህብረተሰቡ  በምግብና መጠጥ  አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እነዚህን ችግሮች  ሲያስተውል በአካልም ሆነ  በ886  ነፃ የስልክ መስመር በመደወል ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበርም  አቶ አባዲ ጠይቀዋል። በአዲስ አበባ ከተማ  የምግብና የመጠጥ አገልግሎት የሚሰጡ 21ሺህ 505 ተቋማት እንደሚገኙ የባለስልጣኑ መረጃ ያመለክታል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም