የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን በፍጥነት ለማሳደግ ማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋትና የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ ይፈልጋል-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን በፍጥነት ለማሳደግ ማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋትና የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ ይፈልጋል-ምሁራን
አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2011 የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት ዕድገት በፍጥነት ለማሳደግና በአገሪቱ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ። የአንድ አገር ማክሮ ኢኮኖሚ ጤናማ ነው የሚባለው የተረጋጋ የግብይት ዋጋና የውጭ ምንዛሬ እንዲሁም ጠንካራ የፋይናንስ ሥርዓት ሲኖር እንደሆነ የመስኩ ምሁራን ይስማማሉ። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባለው የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ መሰረት የወጪ ንግድን የሚያበረታታ ሲሆን አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች በዓይነትና በጥራት ውሱን ናቸው። በሌላ በኩል የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ዝቅተኛ በመሆኑ ለረጅም ጊዜ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩ የልማት ድርጅቶች በከፊል ወደ ግል እንዲዛወሩ ይፋ መደረጉም ይታወቃል። የአገሪቱ የብድር ጫና በመንግስት በጀት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የፈጠረ በመሆኑ በተለያዩ የልማት አውታሮች ላይ መዋል የሚገባው ገንዘብ ለዕዳ ማቃለያ እንዲውል መንግስት እንደተገደደ የምጣኔ ሀብት ምሁራኑ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ያለባትን የብድር ዕዳ ለማቃለል መንግስት የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ማጠናቀቅ እንዳለበትም ጠቁመዋል። በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማቃለል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዲሁም ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ባለሀብቶች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። እንደ ምጣኔ ሀብት ምሁራኑ ማብራሪያ ከወጪ ንግዱ በተጨማሪ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት ላይ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አሰፋ አድማሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ፍላጎትና አቅርቦትን ማጣጣም ያስፈልጋል። በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ዶክተር አጥላው አለሙ በበኩላቸው በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ብዙ ማሻሻያ የሚጠይቁ ጉዳዮች ያሉ ሲሆን በተለይ የዋጋ ግሽበት መቀነስ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት ያመለክታሉ። የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የመንግስት ወጪን መቀነስ፣ በገንዘብ ዝውውር ላይ ቁጥጥር ማድረግና በግብር አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መቀነስም እንዲሁ። የዓለም አቀፉ የፌር ፋክስ ኩባንያ ሰብሳቢና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማምጣት የተጠናከረ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ማካሄድ ይገባል ይላሉ። የግሉ ዘርፍ በኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ እንዲኖረው የተጠናከረ ስትራቴጂ መንደፍ እንደሚገባም በመጠቆም። በአሁኑ ወቅት በምጣኔ ሀብት ያደጉ አገሮች የውስጥ ሰላማቸውን በአስተማማኝ መሰረት ላይ በመገንባት ሙሉ ትኩረታቸውን በልማት ላይ እንዳደረጉ መረጃዎች ያመለክታሉ። የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።