ድርጅቱ የካይዘን የአመራር ፍልስፍናን በመተግበሩ በስድስት ወራት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቱ የካይዘን የአመራር ፍልስፍናን በመተግበሩ በስድስት ወራት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘቱን አስታወቀ
አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2011 የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ባለፉት ስድስት ወራት የካይዘን የአመራር ፍልስፍናን በመተግበሩ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘት መቻሉን አስታውቋል። ገንዘቡ የተገኘው ከድርጅቱ የቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ብቻ እንደሆነም ተገልጿል። በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኪ ማትሱናጋ በበኩላቸው አገራቸው በካይዘን የአመራር ፍልስፍና ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል። አምባሳደሩ ከመንግስት ከፍትኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በካይዘን የአመራር ፍልስፍና የተሰሩ ስራዎችን ጎብኝተዋል። በዚህ ጊዜ አምባሳደር ዳይሱኪ ማትሱናጋ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የካይዘን የአመራር ፍልስፍና በመታገዝ የንግድ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች አሰራር እንዲሻሻል የበኩሉን አስተዋጾኦ እያበረከተ ነው። የአመራር ፍልስፍናው በተለይ በፋብሪካዎች የስራ ቦታን ምቹ በማድረግ፣ ብክነትን በመቀነስ፣ ቀልጣፋና ጊዜ ቆጣቢ አሰራሮች እንዲኖሩ እያደረገ ይገኛል። ውጤቶቹ በድርጅትም እየተመዘገቡ መሆናቸውን አምባሳደሩ ጠቅሰው በቀጣይ ኢትዮጵያ የአመራር ፍልስፍናውን በሁሉም የማምረቻው ዘርፍ ለመተግበርና ለማስፋት የምታደርገውን ጥረት ጃፓን እንደምትደግፍ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ በበኩላቸው ድርጅቱ በቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባለፉት ስድስት ወራት የካይዘን የአመራር ፍልስፍናን መሰረት አድርጎ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል። በዚህም ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘትና ማዳን እንደተቻለ ጠቁመው ሶስት ሚሊዮን ብሩ የተለያዩ ቁርጥራጭ ብረቶችን በሽያጭ በማስወገድና አራት ሚሊዮን ደግሞ አላስፈላጊ ወጪን በመቆጠብ እንደሆነ ተናግረዋል።