የማህፀን በር ካንሰር ክትባት ከመጪው ህዳር ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ይሰጣል

አዲስ አበባ ቅምት 23/2011 ከመጪው ህዳር ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ መከላከያ ክትባት በአገር አቀፍ ደረጃ መሰጠት ሊጀመር መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። ክትባቱ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና በጊዜያዊ የክትባት ማዕከሎች ይሰጣል። የማህፀን በር ካንሰር ክትባት በሙከራ ደረጃ በትግራይና ኦሮሚያ በተመረጡ ወረዳዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል። የማህፀን በር ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡ በሚኒስቴሩ የክትባት ባለሙያ አቶ ጌትነት ባየህ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ክትባቱን ለማስጀመር በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ይሰጣል። ''ከመጪው ህዳር ወር ጀምሮም በአገር አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች ክትባቱ መሰጠት ይጀምራል'' ብለዋል። የማህፀን በር ካንሰር ክትባት መሰጠት ያለበት ከ9 ዓመት ጀምሮ ላሉ ልጃገረዶች ቢሆንም በአለምአቀፍ ደረጃ ባጋጠመው ክትባት እጥረት ምክንያት ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ብቻ ነው የሚሰጠው። ከ30 እስከ 45 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡ ለማህፀን ካንሰር መንስኤ የሆነው ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ምልክት ሳያሳይ ለረዥም ጊዜ በሰውነት ውስጥ የመቆየት አቅም ያለው ሲሆን ቫይረሱ የቅድመ ካንሰር ምልክት ለማሳየት ቢያንስ ከ10 እስከ 15 ዓመታት ይፈጃል፡፡ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር በሽታን ለመከላከል ክትባት አይነተኛና አዋጭ መፍትሄ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ከዚህ ባለፈ ከአቅመ ሄዋን በፊት የግብረ ስጋ ግንኙነት ከመፈፀም መታቀብ፣ ኮንደምን መጠቀምና የማህጸን በር ካንሰር ጫፍ ቅድመ ምርመራ በማድረግ መከላከል ይቻላል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም