ማህበሩ የምስራቅ አፍሪካ የምርምር ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ የምስራቅ አፍሪካ የምርምር ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው
መቀሌ ጥቅምት 23/2011 የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር የምስራቅ አፍሪካ የምርምር ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን የፕሮግራም ማናጀሩ ገለጹ። ማህበሩ ለ37 ሺህ ህሙማን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። ማናጀሩ አቶ አብዱልከሪም ሙሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንዳሉት ማህበሩ ህሙማንን ከመንከባከብ በተጨማሪ የክፍለ አህጉሩ የምርምር ማዕከል ለመሆን እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ይህንንም ለማሳካት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና አግባብ ካላቸው በዓለም አቀፍ ከሚሰሩ የጤና ድርጅቶች ጋር እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። ለማዕከሉ ግንባታ እንዲውል የአዲስ አበባ አስተዳደር በቦሌ ክፍለ ከተማ ሁለት ሺህ ካሬ ሜትር መሬት በነፃ ማግኘቱን ገልጸዋል። ማህበሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ ባቋቋማቸው 60 ቅርጫፎች ለህሙማን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ማናጀሩ ተናግረዋል። ለ37 ሺህ ህሙማን የመድኃኒት አቅርቦት፣እንክብካቤና የሙያ ስልጠና እየሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል። በማህበሩ ከሚደገፉ ህሙማን መካከል 30 ሺህ ያህሉ አዋቂዎች ሲሆኑ፣ሰባት ሺህ ደግሞ ህጻናት መሆናቸውን አቶ አብዱልከሪም ተናግረዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒሰቴር መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለም ላይ 246 ሚሊዮን ሰዎች ከህመሙ ጋር የሚኖሩ ሲሆን፣ህመሙን የመከላከልና መቆጣጠር ተግባራት ካልተጠናከሩ አሀዙ በ2ዐ17 ወደ 38ዐ ሚሊዮን ያሻቅባል ተብሎ ይገመታል፡፡ ህመሙ የሚከሰተው ሰውነት ለኑሮም ሆነ ለእድገት የሚያስፈልገውን ስኳር በትክክል ለመጠቀም ሳይችል ሲቀር ነው፡፡ አንድ ሰው በህመሙ የሚያዘው በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ሲጨምር ነው፡፡ በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን የሚይዘው የስኳር ህመምን ለመቆጣጠር ጤናማ አመጋገብና አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ዋነኞቹ መፍትሄዎች መሆናቸውን መረጃው ይገልጻል።