ቀጥታ፡

በአገር ግንባታ ሂደት የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው -አምባሳደር ራይነር

ጅማ ጥቅምት 23/2/2011 በአገር ግንባታ ሂደት የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ገለጹ፡፡ አምባሳደሩ ትናንት "የነገዪቱን ኢትዮጵያ በመገንባት ሂደት የወጣቶች ሚና" በሚል ርዕሰ  ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንግግር አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፋንታ የሚወሰነው ዛሬ ባለው ወጣቶቿ ስብዕናና ማንነት ላይ  ነው ያላት አምባሳደር ራይነር  "እናንተ ጋር ሳወራ ከወደፊቷ ኢትዮጵያ ጋር እያወራሁ እንደሆነ ይሰማኛል" ብለዋል፡፡ ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት የነበረችው አሜሪካና የአሁኗ አሜሪካ ልዩ መሆናቸውን አስታውሰው፣አሜሪካ ዛሬ ላለችበት ደረጃ የደረሰችው በትናንት ወጣቶቿ ጥረት ነው ብለዋል፡፡ "እናንተም ወጣቶች ጠንካራ ከሆናችሁ የምትመኟትን የበለጸገች ሀገር ባለቤት መሆን ትችላላችሁ" ሲሉም  ወጣቶቹን አሳስበዋቸዋል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ለውጥ ለማሳካት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ ወጣቱ እንደ አገር ለተጀመረው ለውጥ የነበረውን የግንባር ቀደም ሚና በአገር ግንባታ ሂደቱም እንዲደግመው ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች እንደ አሜሪካ ወጣቶች አገራቸውን የሚወዱና በአገራቸው ጥቅም ላይ የማይደራደሩ ዜጎች መሆን እንደሚጠበቅባቸው አምባሳደር ራይነር አሳስበዋል፡፡ የአሜሪካ መምህራን በእንስሳት ህክምናም ሆነ በሌሎች የትምህርት ዘርፎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት እያስተማሩ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያን  ተማሪዎች በአሜሪካ የትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው አገራቸውን የሚያገለግሉበት አሰራር መኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ መንግሥታቸው የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማሟላት በተለያዩ ዘርፎች ድጋፉን እንደሚያጠናክር አምባሳደር ራይነር አረጋግጠዋል፡፡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ  የስድስተኛ ዓመት የህክምና ተማሪ ደመላሽ ሰይፈዲን አሜሪካ የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት እንድትደግፍ ጠይቋል፡፡ በወጣቱ ግንባር ቀደም መሪነት የተጀመረው የለውጥ ሂደት ቀጣይነት እንዲረጋገጥ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል፡፡ በጅማ ዩኒቨርስቲ የአምስተኛ ዓመት የእንስሳት ህክምና ተማሪ ይመስገን ታረቀኝ በኩሉ የእንስሳት ሀብት ዘርፍ ልማትን ለማሳደግ ከአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ እንደሚጠብቅ ገልጿል፡፡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ አምባሳደሩ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ልምዳቸውን ማካፈላቸው ወጣቶች አገራቸውን እንዲውዱና ለለውጥ ጠንክረው እንዲሰሩ መነቃቃትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም