በደቡብ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት የክልሉ መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት የክልሉ መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተመለከተ
ሀዋሳ ጥቅምት 23/2011 በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አባላት አመለከቱ፡፡ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ አባላቱ እንዳሉት በክልሉ እስካለፈው ሰኔ ወር ድረስ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሰላማዊ ሁኔታ የነበረ ቢሆንም ከዚያ ወዲህ ግን የጸጥታ ችግር ተከስቷል፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ዱጸ ታምሩ በሰጡት አስተያየት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት የተወሰደው የመፍትሔ እርምጃ በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች የክልሉ መንግስት ሄዶ እየጠየቀ ያለው በሰው ህይወትና ንብረት ጉዳት ከደረሰ በኋላ እንደሆነ ጠቁመው ይህን በተመለከተም ሪፖርቱ ያለውን ችግር በሚገባ እንዳላሳየ ተናግረዋል፡፡ ችግሮች ተባብሰው የከፋ ችግር ከመድረሱ በፊት እስከ ስፍራው ድረስ ተወርዶ መስራት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች ሰብዓዊ መብታቸውና ክብራቸው እየተነካ የመንግስት መኖርና አለመኖር ጥርጣሬ እያደረባቸው እንደሚገኝ የህዝብ ጥያቄ ይዘው የመጡ ጭምር የሚታሰሩበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል፡፡ በጋሞጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳና ከባስኬቶ ልዩ ወረዳ መሀል ባሉ ቀበሌዎች ከማንነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡ የአማሮ ወረዳ ተወካይ አቶ እልኩ ወንድማገኝ በበኩላቸው በክልሉ የህዝቦችን አንድነት የሚሸረሽሩ ሁኔታዎች እንደተፈጠሩና የህዝቡ ሰላም እየታወከ ችግር ውስጥ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ተወካዩ እንዳሉት በአማሮና ቡርጂ ወረዳ ከአጎራባች ጉጂ ዞኖች የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ኃይል በሚያደርሰው ጥቃት የሁለቱ ወረዳ ህዝቦች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደተዳረጉ ነው፡፡ ማንነትን ምክንያት የሚያደርጉ ችግሮችን የመኮነንና የማውገዝ ሁኔታ እንደማይታይ ጠቁመዋል፡፡ ሌላው የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ አስቴር ጉች ከሱርማ ወረዳና ከአጎራባች የሱዳን ቶፓሳ ጎሳ ሱርማ ላይ ሱርማ ደግሞ ከዲዚ ጋር ያለው ግጭት ለህዝቡ ስጋት እየሆነው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት በመሬት ጥበት ወደ ካፋ ዞን ሄደው የሰፈሩ የዞኑ ተወላጆች በጸጥታ ችግር ተሰደው እየተመለሱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከምባታ ጠንባሮ ተወካይ አቶ አስቻለው አበበ ናቸው፡፡ ይህን ችግር ለማረምና ለማስተካከል የሚደረግ ጥረት እየታየ እንዳልሆነ ጠቁመው " ባለፈው ዓመት እንደ ሀገር በበርካታ ቦታዎች ላይ ችግሮች ሲስተዋሉ ሰላማዊ የነበረው ክልሉ ብቻ እንደነበርና ይህንንም አምና አድንቀን አልፈናል "ብለዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በሰጡት ምላሽ ከምክር ቤቱ አባላት የተነሱት ጥያቄዎች ትክክል መሆናቸውንና ችግሮቹን ለመፍታት እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በአማሮና ቡርጂ ወረዳ አካባቢ የተነሱ ችግሮችን በተመለከተ ከፌዴራልና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ከጌዴኦ ዞን ጋር በተያያዘ ከአጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች ብዛት ያለው ህዝብ ከአካባቢው እንደተፈናቀለና ለመመለስ የተከናወኑ ስራዎች ቢኖሩም ከተመለሱ በኋላም ችግሮች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ ከቤንች ማጂ ዞን የተነሳው ችግር ከአጎራባች ሱዳን በመነሳት በአካባቢው ባሉ አርብቶ አደሮች መካከል ያለውንም ችግር ለመፍታት በበጀት ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ በማካተት በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ከክልሉ ማዕከላዊ ዞኖች በሰፈራ ወደ ካፋ ዞን በሄዱ ላይ በተያዘው ዓመት የተነሳ ግጭት እንዳለና ችግሩን ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ በባስኬቶ ልዩ ወረዳና በጋሞጎፋ ዞን መሎኮዛ ወረዳ ጋር በተያያዘ የተነሳው ጉዳይ በጥንቃቄ መታየት ያለበት መሆኑንና ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ሲቻል የተሄደበት መንገድ ተገቢ ባለመሆኑ ጉዳዩ እየተጣራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የምክር ቤቱ ስምንተኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉ መንግስትን የ2010 በጀት ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት ዙሪያ ከመከረ በኋላ በአራት ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡