በምዕራብ ሸዋ ዞን ከመደበኛ ሰብል ልማት ጎን ለጎን በቡና ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን ከመደበኛ ሰብል ልማት ጎን ለጎን በቡና ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው
አምቦ ጥቅምት 23/2011 ከመደበኛ ሰብል ልማት ጎን ለጎን የቡና ልማት በማካሄድ ተጠቃሚ መሆናቸውን በምዕራብ ሸዋ ዞን የባኮ ቲቤና የዳኖ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ። በወረዳው የድሬዳኖ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኩመሳ አዱኛ በሰጡት አስተያየት ባለፉት 12 ዓመታት ከሰብል ልማት በተጓዳኝ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ በሚያካሂዱት የቡና ልማት ተጠቃሚ ሆነዋል። በየዓመቱ ከቡና ምርት ሽያጭ 80 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ባለ 65 ቆርቆሮ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ከመስራት ባለፈ ጥሪት ማፍራታቸውን ገልጸዋል። በወረዳው የድሬ ሃረዩ ቀበሌ አርሶ አደር ሹመት ቴሶ በበኩላቸው አንድ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ ቡናን በማልማት በዓመት እስከ 12 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከቡና ልማት ገቢ ሁለት ልጆቻቸውን በከተማ ቤት ተከራይተው በማስተማር ላይ መሆናቸውን የገለጹት አርሶአደሩ የመጀመሪያ ልጃቸውንም እየረዱ ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ለማስመረቅ መቻላቸውን ነው የጠቆሙት። ዘንድሮም ልማቱን አጠናክረው መቀጠላቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ ባለፈው ክረምት በ1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የተከሉትን ምርጥ የቡና ችግኝ በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። "የቡና ልማት የሕይወቴ መሰረት ነው " ያሉት ደግሞ በባኮ ቲቤ ወረዳ ኦዳሃሮ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ነገሠ ባልቻ ናቸው። በየዓመቱ በቡና ከሚያለሙት አንድ ሄክታር መሬት ከ80 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ ገልጸው የገቢ ምንጫቸውን ለማስፋት በባኮ ቲቤ ከተማ በ400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ስድስት ክፍል መኖሪያ ቤት ሰርተው እያከራዩ መሆናቸውን ገልጸዋል። "ዘንድሮ የቡና ልማቱን ወደ ሁለት ሄክታር ለማስፋፋት አቅጄ እየሰራሁ ነው" ብለዋል። በምዕራብ ሸዋ ዞን የቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን ጽህፈት ቤት የቡና ልማት ኤክስቴንሽን ባለሙያ አቶ ገዛኸኝ ጀርመን በበኩላቸው እንደገለጹት በዞኑ በ13 ወረዳዎች እየተካሄደ ባለው የቡና ልማት ከ12 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ተጠቃሚ ሆነዋል። ልማቱን ለማስፋፋት በተደረገው እንቅስቃሴ በ2010/2011 የምርት ዘመን አዲስ በለማው 731 ሄክታር መሬት ላይ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ተተክሎ በአርሶ አደሩ እንክንካቤ እየተደረገለት መሆኑን አስረድተዋል። በምዕራብ ሸዋ ዞን እስካሁን 4 ሺህ 800 ሄክታር መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ ሲሆን በየዓመቱም ከ7 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።