ኤጀንሲው የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖችን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖችን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ገለጸ
አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2011 የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች ያለባቸውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታትና ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ እርምጃዎች እንደሚወስድ አስታወቀ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች የተመሰረቱበትን ዓላማና ግብ ስለማሳካታቸው፣ ለአባላቱና በአጠቃላይ ለሸማቹ ህብረተሰብ እያስገኙት ያለውን ጠቀሜታ፣ ያለባቸውን ማነቆ የሚፈትሽ እና ሸማቾች በዩኒየኖቹ ያላቸውን እርካታ የሚገመግም የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል። የጥናቱ ግኝት ትናንት በአዲስ አበባ ሲቀርብ እንደተገለጸው፤ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች የዘይት፣ ስኳር፣ ዱቄትና ጤፍ ምርቶች ላይ የአቅርቦትና የስርጭት ችግር ይታይባቸዋል። የአቅርቦትና ስርጭት ችግር ከሚታይባቸው ምርቶች መካከል በዋናነት ድጎማ የሚደረግባቸው ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ ጥናቱ አሳይቷል። ችግሩ የጎላ ባይሆንም ስንዴ፣ ምስር፣ ፓስታ፣ መኮረኒ እና የመሳሰሉት ምርቶች ላይም የአቅርቦትና የስርጭት ችግር እንዳለ ጥናቱ አመላክቷል። ለአቅርቦትና ለስርጭት ችግር ዋናኛ መንስኤዎች የካፒታል እጥረት፣ ተፈላጊ ምርቶችን በሚፈለገው ደረጃና መጠን ማግኘት ያለመቻልና የዋጋ ንረት መሆናቸውን ጥናቱ ተለይቷል። አብዛኞቹ ዩኒየኖች የጅምላ ምርቶችን ከሞላ ጎደል በትክክለኛና ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ለአባላቱ እያዳረሱ መሆኑን ያመላከተው ጥናቱ ምርት በበቂ መጠን ያለማቅረብ፣ ውል ከተገባ በኋላ ምርቶችን በውሉ መሰረት ያለማቅረብና የሽያጥ ዋጋ በየጊዜው መቀያየር የዩኒየኖቹ ችግር እንደሆነ ተገልጿል። ምርት ለአባላቱ ሳይዳረስ አልቋል መባሉ፣ በሚፈለገው መጠንና የጥራት ደረጃ አለመቅረባቸው፣ ምርቶቹ በሚፈለገው መንገድ ለአባላቱ እየተሰራጩ ላለመሆናቸው መገለጫዎች መሆናቸው ታውቋል። ጥራትና ደህንነታቸው የተረጋገጠ ምርቶች እንዲቀርቡ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበትም የጥናቱ ግኝት አመልክቷል። የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች አባላቱ የሚፈልጓቸውን የተለያዩ የፋብሪካም ሆነ የግብርና ምርት አይነቶችን ከማቅረብ አኳያ ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው ተጠቁሟል። አብዛኞቹ ዩኒየኖች ማህበራቱ ከሚፈልጓቸው የምርትና የሸቀጣ ሸቀጥ አይነቶች አኳያ የአባላትን እርካታና ፍላጎት እንዳላሟሉ የሚያምኑ መሆናቸውን መጠቆማቸውን በጥናቱ ተዳስሷል። ''የዳሰሳ ጥናቱ ግኝት የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ከሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች ምርቶችን በሚፈልጉት ሰዓትና ጊዜ አልፎ አልፎ ብቻ ያገኛሉ ሲል ጥናቱ ይገልጻል። የሸማቾች ዩኒየኖች ዋና አላማ ትርፍ ሳይሆን ምርቶችን በቀጥታ ከአምራቾች በመረከብ በተመጣጣኝ ዋጋ ለአባሎቻቸው በጅምላ ማቅረብ እንደ መሆኑን መጠን የሚቀርቡ ምርቶች የዋጋ ሁኔታ ከሌሎች የገበያ ዋጋዎች ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑንም አሳይቷል። ዩኒየኖቹ በምርቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረትና የአቅርቦት ችግርን በመፍታት ረገድ መጠነኛ ሚና እንዳላቸው ተገልጿል። ዩኒየኖቹ ያለባቸውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታትና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል እንዲሁም በጥናቱ የተመላከቱ ክፍተቶችን ለማስተካከል የተለያዩ እርምጃዎች እንደሚወሰድ የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው አሊ ገልጸዋል። ዩኒየኖቹ ያለባቸውን የካፒታል እጥረት በመፍታት የሸማቹን ፍላጎት የሚያረካ የምርት አቅርቦት እንዲኖራቸው ለማስቻል የአባላት መዋጮን በአግባቡ የማሰባሰብና ከሌሎች ህብረት ስራ ኤጀንሲዎች ብድር ለማግኘት እንደሚሰራ ጠቁመዋል። የሸቀጣ ሸቀጥ ደህንነትን ለማስጠበቅና ምርትን በሚፈለገው ጊዜ፣ ጥራትና መጠን ለማቅረብ ጥንቃቄ የተሞላበት ስራ ይሰራልም ነው ያሉት። ዩኒየኖቹ ከአሰራርና ከመልካም አስተዳደር ጋር የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመሙላት የተማሩ ባለሙያዎችን እንደሚቀጥሩ ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል። በአዲስ አበባ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን አባላት ያሏቸው ከ11 ሺህ በላይ የህብረት ስራ ማህበራት ይገኛሉ።