አንበሳ የከተማ አውቶብስ በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማቋረጡ ተቸግረናል- ተገልጋዮች

14
ጥቅምት 23/2011 በረጅም ዘመን አገልግሎቱ የሚታወቀው አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት በተወሰኑ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማቋረጡ ለትራንስፖርት እጥረት መጋለጣቸውን ተገልጋዮች ተናገሩ፡፡ የኢዜአ ሪፖርተር በኮልፌ ቀራንዮ፣ ቀጨኔ፣ ሚኪሊላንድና መሰል አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች እንዳሉት አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት በነዚህ አካባቢዎች ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት  በማቋረጡ ለችግር ተዳርገዋል፡፡ የቀጨኔ አካባቢ ነዋሪዋ ወይዘሮ ባዩሽ ለማ  ከሰፈራቸው  እስከ መርካቶ በሁለት ብር የምታደርሳቸው ስምንት ቁጥር አውቶብስ አገልግሎት በማቋረጧ ለተጨማሪ ወጪና እንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በሚኪሊላንድ የጋራ መኖሪያ ቤት የሚኖሩት መምህር  በላቸው አንዳርጌም ከሚኖሩበት አካባቢ ተነስተው ወደ መርካቶና ፒያሳ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አውቶብሶች አገልግሎት በማቋረጣቸው ህብረተሰቡ ለችግር መዳረጉን ገልጸዋል፡፡ መምህር በላቸው እንዳሉት አገልግሎቱ በተለይ  ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚሰጠው የተመጣጠነ አገልግሎት በተጨማሪ ለተማሪዎችና መንግስት ሰራተኞችም የጎላ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አንበሳ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አሰራሩን በማሻሻል ቀልጣፋና ዘመናዊ አሰራርን መሰረት ያደረገ አገልግሎት በመስጠት ፋንታ የአገልግሎት መስመሮቹን መዝጋቱ ተገቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በአስኮ የአዲስ ሰፈር ነዋሪው  ወጣት ሳሙኤል መንገሻ  በአካባቢው በተለይ ጠዋትና ማታ ህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገረ መሆኑን ገልጾ ከአስኮ አዲስ ሰፈር አገልግሎት ለመስጠት የተመደበችው አውቶብስ ስራ ማቆሟ  ችግሩን እንደሚያባብሰው ተናግሯል፡፡ ከስድስት ኪሎ በሩፋዔል አስኮ እንዲሁም ከስድስት ኪሎ በሜክሲኮ ቄራ ይመላለሱ የነበሩትን አውቶብሶች ለማግኘት መቸገሩን የተናገረው ደግሞ ተማሪ ያለው ደምሴ ነው፡፡ ይህም በተለይ የማታ ትምህርት ለመከታተተል የትራንስፖርት እጥረቱን እንዳባባሰው ነው የተናገረው፡፡ በአንበሳ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የብዙሃን ትራንስፖርት ዋና ስራ ሂደት ተጠባባቂ ሃላፊ አቶ መላኩ ካሳዬ የነዋሪዎቹ ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑን አምነዋል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ የተፈጠረው  የአገልግሎት መስመሮች በመታጠፋቸው ሳይሆን  በርካታ አውቶብሶች በእርጅና ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው መሆኑን  አብራርተዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታ ድርጅቱ  ሰባት መቶ አውቶብሶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ከመጪው ሰኞ ጀምሮ አዳዲስ አውቶብሶችን እንደሚረከብም ገልጸዋል፡፡ አሁን ያሉትን አውቶብሶች በአግባቡ በመጠቀም ችግሩን ለማቃለል ጥረት እደሚደረግም ነው ኃላፊው የተናሩት፡፡ አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት በአሁኑ ወቅት 444 አውቶብሶችን በየቀኑ እያሰማራ ቢሆንም ከ20 በላይ የሚሆኑት አውቶቢሶች  በብልሽትና በቴክኒክ ጉድለት ሳቢያ በየቀኑ በአግባቡ ስራ እንደማይሰሩ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም