ቀጥታ፡

የንግድ ትርኢቶች መዘጋጀት በአምራችና ተጠቃሚ መካከል ዘላቂነት ያለው የደንበኝነት ትስስር ለመፍጠር ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2011 የንግድ ትርኢቶች መዘጋጀት አምራቾች የሚያመርቷቸውን ምርቶች ተጠቃሚዎች እንዲያውቁና ዘላቂነት ያለው የደንበኝነት ትስስር እንዲፈጥሩ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑ ተገለጸ። ''የኢትዮጵያን ይግዙ" የሚል መሪ ሀሳብ ያለው 11ኛው ኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ዛሬ በአዲስ አበባ የኤግዚቢሽን ማዕከል ተጀምሯል። የንግድ ትርኢቱ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ የንግድ ድርጅት ተወካዮች፣ ተጋባዥ እንግዶች እንዲሁም ጐብኝዎች በተገኙበት ተከፍቷል። ኢዜአ በንግድ ትርኢቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የአገር ውስጥ ድርጅቶችን አነጋግሯል። የዲኤች ገዳ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የብርድ ልብስ ፋብሪካ የሽያጭ ተቆጣጣሪ አቶ ሽመልስ ጌታቸው ድርጅታቸው ከዚህ በፊት በነበሩት 10 የንግድ ትርኢትቶች ላይ መሳተፉን ይገልጻሉ። በዚህ ንግድ ትርኢት ላይ መሳተፍ ያለው ዋንኛ ፋይዳ የምናመርታቸውን ምርቶች የሚገዛ ተጠቃሚዎችን በማግኘት ምርትን ማስተዋወቅ እንደሆነ ተናግረዋል። በተጨማሪም በንግድ ትርኢቱ ላይ የሚሳተፉ የውጭ አገር ኩባንያዎች ጋር በመገናኘት በቀጣይ በትብብር በሚሰራበት በተለይም በሽርክና ለመስራት ድርጅታቸው ጥረት እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል። ድርጅቱ ከተለያዩ አገራት ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር ከውጭ የሚያመጣቸውን ምርቶች ኩባንያዎቹ እዚሁ በማምረት እንዲያቀርቡ የሚቻልበት ሁኔታም ላይ ምክክር እንደሚያደርጉም ጠቅሰዋል። የቴክኖስታይል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ዳይሬክተር ልዩ ረዳት አቶ ደረጀ መንገሻ በበኩላቸው የንግድ ትርኢቱ ከደንበኞች ጋር ለመተዋወቅና ትስስር ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንዳለው ያነሳሉ። በንግድ ውስጥ ዋንኛ ባለድርሻ የሚባሉትን አምራች ኢንዱስትሪዎችንና ሸማቹን ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንጻርም ያለው ጠቀሜታ ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል። በቀጣይ በሚደረጉ የንግድ ትርኢቶች ላይ በአንድ ዘርፍ የሚሳተፉ ኩባንያዎች ቁጥር ቢያድግ በድርጅቶች መካከል የልምድ ልውውጥ ያደርጋል ብለዋል። የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ እንዳሉት ዛሬ የተጀመረው የንግድ ትርኢት ተሳታፊዎች ጠንካራ ትስስር መፍጠርና የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ኩባንያዎች በሽርክና እንዲሰሩ የቢዝነስ አማራጭ ለመፍጠር የሚያስችል ነው። ንግድ ትርኢቱ ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ምርትና አገልግሎታቸውን ምርታቸውን ለሚፈልጉ ደንበኞች በማስተዋወቅ ዘላቂነት ያለው የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩ ያስችላል ብለዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለውጭ ኩባንያዎች በማስተዋወቅ አገር በቀል ምርቶች እንዲሸጡና ተቀባይነት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል። በንግድ ትርኢቱ ማብቂያ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የሚያገናኝ የቢዝነስ ለቢዝነስ ትስስር መድረክ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ዛሬ የተጀመረውና መሰል የንግድ ትርኢቶች መዘጋጀት ንግድና ኢንዱስትሪን ለማሳደግ እንደሚጠቅሙ ገልጸዋል። ጠንካራ የአገር ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እንዲኖርና በኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ ድርሻ ሊያደግ እንደሚገባና ይህን ማድረግ ከታቸለም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻላል ብለዋል። 11ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎችን ከተጠቃሚዎች ጋር እያገናኘ እስከ ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚቆይ ተገልጿል። ንግድ ትርዒቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ የንግድ ድርጅቶች ይሳተፉበታል ተብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም