ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ ህገወጥ መድሃኒቶች ወደ አገር ገብተው መሰራጨታቸውን አስታወቀ

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2011 የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ቪጎ እና ቬጎ የሚባሉ ህገ ወጥ የመድሃኒት አይነቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው እየተሸጡ መሆኑን አስታወቀ። በባለስልጣኑ የመድሃኒት ተቋማት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ እንዳለ እንዳመለከቱት፤ የመድሃኒት አይነቶቹ ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠና በባለስልጣኑ ሳይመዘገቡ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ናቸው። 'ለስንፈተ ወሲብና ለደም ግፊት' በሚል ህገ ወጥ በሆነ መንገድ እየተሸጡ የሚገኙት መድሃኒቶቹ በከፍተኛ ሁኔታ በአገር ውስጥ መሰራጨታቸውን አስታውቀዋል። በተለይም በኮምቦልቻ፣ በደሴ፣ በጎንደርና በአዲስ አበባ መድሃኒቶቹ ገብተው እየተሸጡ መሆናቸው መረጋገጡን አመልክተዋል። ባለስልጣኑ ህገ ወጥ መድሃኒቶችንና አዘዋዋሪዎችን ለመያዝ ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡም እንዲተባበር ጠይቀዋል። እነዚህ መድሃኒቶች ሲሸጡ የተመለከተ አካል በ8082 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል ጥቆማ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ማንኛውም ግለሰብ መድሃኒት በሚገዛበት ጊዜ የሚገዛው መድሃኒት በባለስልጣኑ መመዝገቡን www.mris.fmhaca.gov.et ድረ ገጽን በመጠቀም ማወቅ እንደሚችል ጠቁመዋል። ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመሆን ህገ ወጦችን ለመያዝ በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ያለ ሃኪም ትዛዝ የሚሸጡ መድሃኒቶች ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠና የጎንዮሽ ጉዳታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ በየትኛውም መንገድ ከመግዛት እንዲቆጠብና ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አቶ ገዛኸኝ አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም