ቀጥታ፡

ማዕከሉ ለአሶሳና አካባቢው አርሶ አደሮች የሙዝ ዝርያ እያሰራጨ ነው

አሶሳ ጥቅምት 22/2011 የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ለአካባቢው አርሶ አደሮች የሙዝ ዝርያ እያሰራጨ መሆኑን አስታወቀ፡፡ አሶሳና አካባቢው ለሙዝ ልማት የሚስማማ አየር፣ለም መሬትና ውሃ አለው፡፡ እነዚህን ምቹ  ሁኔታዎች በማቀናጀት ልማቱን ለማካሄድ እንደሚቻል ይታመንበታል። ይሁንና ምርቱ በሚገባ ባለመልማቱ የጥራት ደረጃው ዝቅተኛ የሆነ አንድ ፍሬ ሙዝ ከሦስት ብር እስከ ስድስት ብር እየተሸጠ ነው። የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ጊዲሳ እንደሚሉት ማዕከሉ ከሚያከናውናቸው ምርምሮች መካከል አካባቢው ለሙዝ ተክል ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ አንዱ ነው፡፡ ለዚህም የአካባቢውን የሙዝ ምርት በምርምር ማሻሻል፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተለቀቁ ዝርያዎችን በማላመድና ዝርያዎችን ያዳቅላል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ “ ዊሊያም ” የተባለው ዝርያ በሄክታር እስከ 42 ኩንታል እንደሚያስገኝ መረጋገጡን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ዝርያው ለአርሶ አደሮችና ለአርሶ አደር ማህበራት እየተሰራጨ መሆኑን አስረድተዋል።በሰፋፊ እርሻ ልማት ለሚሳተፉ ባለሃብቶችም ለማቅረብ ይቻላል ብለዋል፡፡ ማዕከሉ የሙዝና ሌሎች ምርምር ሥራዎችን በስፋት በመስኖ ለማልማት ያጋጠመውን የመሬት እጥረት የክልሉ መንግሥት እንዲፈታለት ጠይቀዋል፡፡ ወይዘሮ ዘሙ ሰይድ ሙዝ የሚያለሙ አርሶ አደር ናቸው።በአካባቢው የሙዝ ዋጋ ውድ ቢሆንም፤ አርሶ አደሩ ለተክሉ የሚያደርገው እንክብካቤ ዝቅተኛ ነው ይላሉ፡፡ አርሶ አደሩ አሁን ከሙዝ  የሚያገኘው ጥቅም እንዲጨምር ግንዛቤው ማሳደግና ዝርያውን ማሻሻል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በአሶሳ ወረዳ ፍራፍሬ፣ የጓሮ አትክልትና ሰብል የሚያመርተው የጋመዩ የመስኖ ኅብረት ሥራ ማህበር ሙዝ ከአካባቢው አልፎ እስከ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ራዕይ አለው፡፡ ራዕዩን ለማሳካት ከማዕከሉ ያገኙትን የተሻሻለ የሙዝ ዝርያና ስልጠና በመጠቀም በመስኖ እያለሙ መሆናቸውን የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ አጠይብ ፊለል ገልጸዋል፡፡ የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ከተቋቋመ 12 ዓመታት  እስካሁን ከ32 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የተሻሻሉ የሰብል፣ የእጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም