ለሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደቱ የበኩላችንን ኃላፊነት እንወጣለን- በሰመራ ዩኒቨርስቲ የአፋር ክልል ተወላጅ ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደቱ የበኩላችንን ኃላፊነት እንወጣለን- በሰመራ ዩኒቨርስቲ የአፋር ክልል ተወላጅ ተማሪዎች

ሰመራ ጥቅምት 22/2011 ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሰመራ ዩኒቨርስቲ ተመድበው ለሚማሩ ተማሪዎች ድጋፍና አንክበካቤ በማድረግ ለሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደቱ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ በዩኒቨርስቲው የሚማሩ የክልሉ ተወላጆች ገለጹ፡፡ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ለሰመራ ዩኒቨርስቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች የኃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የአንኳን ደህና መጣችሁ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ በሰመራ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ የአፋር ክልል ተወላጆች ለኢዜአ እንደገለጹት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ሰመራ ዩኒቨርስቲ ተመድበው ለሚመጡ ነባርም ሆነ አዲስ ተማሪዎች ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ ለሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደቱ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ተወላጅና የሰመራ ዩኒቨርስቲ የ2ኛ አመት ተማሪ የሆነው አቡበከር ዑመር ከተለያዩ አካበቢዎች በዩኒቨርስቲው ለተመደቡ ነባርና አዲስ ገቢ ተማሪዎች ደማቅ አቀባበል ማድረጋቸውን ተናግሯል፡፡ ተማሪዎቹ በዩንቨርስቲው በሚኖራቸዉ ቆይታ የአፋር አንግዳ ተቀባይነትና አክባሪነት ባህልን በሚመጥን አግባብ ድጋፍና እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የጠቆመው ተማሪ አቡበከር "ይሄም ተማሪዎችን ቤተሰባቸው መሃል ያሉ ያክል እንዲሰማቸው ያደርጋል"ብሏል፡፡ የአካባቢው ተወላጅና የመጀመሪያ አመት ተማሪ የሆነው ሙሳ መሐመድ ምንም አንኳን ለዩኒቨርስቲው አዲስ ቢሆንም የአካባቢዉ ተወላጅ በመሆኑ ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎችን መንከባከብና የመርዳት ኃላፊነት እንዳለበት ተናግሯል፡፡ ከዩኒቨርስቲው ውጭ በሰመራም ሆነ ሎግያ ከተማ ተማሪዎች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የአካባቢውን ህብረተሰብ ባህልና ወግ ተረድተው ሰላማዊ ግንኙነት አንዲኖራቸው አስፈላጊውን መረጃ በመስጠትና አቅጣጫ በመጠቆም ኃላፊነቱን አንደሚወጣ አስታውቋል፡፡ የ3ኛ አመት ተማሪ የሆነውና የክልሉ ተወላጅ ተማሪ ሲራጅ አህመድ በበኩሉ ተማሪዎቹ በቆይታቸው ወቅት ችግሮች በሚያጋጥማቸው ጊዜ ከሌሎች የክልሉ ተማሪዎች ጋር በመሆን ፈጥኖ ደርሶ ከመርዳት ባለፈ የዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ሰላማዊ አንዲሆን ኃለፊነቱን አንደሚወጣ ገልጿል፡፡ በአካባቢው ነዋሪና በዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ መሆናቸውን አዲስ ገቢ ተማሪዎች ገልጸዋል፡፡ ከአማራ ክልል ወደ ሰመራ ዩኒቨርስቲ ተመድቦ የመጣው አዲስ ገቢ ተማሪው እንድሪስ ሁሴን በዩኒቨርስቲው ማህበረሰብና በክልሉ ነዋሪዎች የተደረገለት አቀባበል ከጠበቀው በላይ መሆኑን ተናግሯል፡፡ የአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ፍጹም ፍቅርና ወንድማማችነት የተሞላበት መሆኑን የጠቆመው ተማሪ እንድሪስ "ይሄም በአጭር ግዜ ውስጥ ዩኒቨርስቲውን ለመላመድ ያግዘኛል" ብሏል፡፡ በቆይታውም ከሌሎች ዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ጋር በመከባባርና በመተሳሰብ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ኃላፊነቱን አንደሚወጣ ተናግሯል፡፡ ከደቡብ ክልል የመጣው ተማሪ ጥበቡ በቀለ በበኩሉ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብና የአካባቢው ነዋሪዎች አስከ አዋሽ 7 ድረስ በመምጣት ያደረጉላቸው አቀባበል እጅግ አስደሳች መሆኑን አስረድቷል፡፡ ይሄም ትምህርቱን ያለምንም ስጋት ተረጋግቶ እንዲማርና የትምህርት አመቱን በስኬት ለማጠናቀቅ እንደሚያስችለው ተናግሯል፡፡ የሰመራ ዩኒቨርስቲ ዘንድሮ የተቀበላቸውን ከ3ሺ 500 በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ7ሺ 500 በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያስተምራል፡፡ የሰመራ ዩኒቨርስቲ ጥቅምት 19ና ጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡