ማህበሩ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀ
ደብረ ብርሃን ግንቦት 14/2010 በተለያየ ምክንያት ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስታወቀ። ማህበሩ በሰሜን ሽዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ የከፈተው የህዝብ መድኃኒት ቤት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። መድኃኒት ቤቱ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ለማብሰር በተዘጋጀው ስነስርአት ላይ የማህበሩ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ወንድአለ አባዜ እንዳሉት በኢትዮጵያ ከ 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች አሉ። ለነዚህ ወገኖች ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ መንግስት ማስታወቁን ተከትሎ ማህበሩ የበኩሉን ለማገዝ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል። "ለእዚህም ማህበሩ 10 ሚሊዮን ዶላር የማሰባሰብ ሥራ ጀምሯል" ያሉት ምክትል ዋና ፀሐፊው፣ እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማግኘት መቻሉን አቶ ወንዳለ አስታውቀዋል። ድጋፉ ከኔዘርላንድስ፣ አውስትራሊያ፣ ዴንማርክ፣ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌደሬሽንና ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የተገኘ መሆኑን ጠቁመው፣ ቀሪውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። "በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ በድርቅ ለተጎዱ፣ በተለያዩ ጊዜያት ተከስተው በነበሩ ቀውሶች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የአልባሳትና ሌሎች ድጋፎች እየተደረገ ነው" ብለዋል። በተለይም ዕድሜያቸው አምስት ዓመትና ከዚያ በታች ለሆኑ 140 ሺህ ሕጻናት፣ ነፍሰጡርና ለሚያጠቡ እናቶች የአልሚ ምግብ እንዲያገኙ መደረጉን ነው የገለጹት። እንደአቶ ወንዳለ ገለጻ በደቡብ ክልልና በኦሮሚያ አካባቢዎች 175 ሺህ 464 ሰዎችን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በሀገር ውስጥ በነበሩ ግጭቶች ለተፈናቀሉ ወገኖችም ማህበሩ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑንም አመልክተዋል። ማህበሩ ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ሌሎች ሰዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሕብረተሰቡ በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በሰሜን ሽዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ ቀደም ሲል በሕብረተሰቡ ተሳትፎ የተሰራውን ቤት ማህበሩ ለሕዝብ መድኃኒት ቤት እንዲያገለግል 900 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል። በትናትናው እለት መድኃኒት ቤቱን ከማስጀመር ባለፈ ለአካባቢው አገልግሎት የሚሰጥ አንድ አምቡላንስም በስጦታ አበርክቷል። የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገበረፃደቅ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጎን ሆኖ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። "በቀጣይም ማህበሩ ከዚህ የተሻለ ማህበራዊ ድጋፍ ለማድረግ አዳዲስ አባላትን ለማፍራት ለሚደረገው ጥረት አስተዳደሩ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል "ብለዋል። የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥላሁን ጸጥአርጌ በበኩላቸው አካባቢው ቆላማ በመሆኑ ህብረተሰቡ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭ መሆኑን አመልክተዋል። በአካባቢው ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የሚሰጥ የህዝብ መድኃኒት ቤት ባለመኖሩ ነዋሪዎች መድኃኒት ፍለጋ ደብረብርሃን ከተማ ድረስ በመሄድ ለእንግልትና ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል ። "መድኃኒት ቤቱ በከተማው መከፈቱ ሕብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ ፈዋሽ መድኃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ያስችለዋል" ብለዋል። በመድኃኒት ቤቱ መክፈቻና በአምቡላንስ ርክክብ መርሃ ግበሩ ላይ የከተማው ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።