ቀጥታ፡

አልጠግብ ባይ…

በሰውነት ጀምበሩ ( ኢዜአ) እንዴት እንዴት ናችሁ? አንዳንድ ቀን የለም? ድብርና ድብትብት የሚያደርጋችሁ? እንዲያ ባለው ቀን ምን ሆነ መሰላችሁ? መቼም ቶሎ ወደ ገደለው እየገባን ካልተጫወትን ነዳጁን አንችለው። አሉባልታና ወሬ ሲሆን ያልተሳቀቅን ደግሞ ለቁም ነገር አትሉኝም? ታዲያስ! ዛሬ ትንሽ በባህረ ሀሳብ  ነው የማጫውታችሁ። አደራ እናንተም እንደዋልጌው በየፌስቡኩ ገጽ የስድብና የዘረኛ አስተያየት ካልሆነ አናነብም የሚል ትክትክ እንዳይጋባባችሁ ጠንቀቅ በሉ። ምን ይታወቃል ዘንድሮ የሥጋ ሕመሙ ወደ መንፈስ፣ የመንፈሱ ወደ ሥጋ እየተቀያየረ ነው እኮ ያስቸገረን። ዋሸሁ እንዴ? ‹‹እኔን ያሰኘኝ ፍቺው ፍቺው...›› አለች አሉ ዘፋኟ፡፡ ገር ልብ ያለው ሰው ድሮም መጨረሻው ፍቺ እንጂ አብሮነት አይሆን። ገር አገር ሲያጣም ዕጣው ተመሳሳይ ነው። ‹‹ዕድል የቢራ ቆርኪ ያህል አታዝንልህም፤›› አለኝ አንድ ወዳጄ። አዲሱን ዓመት በቆርኪ መልካም ፈቃድ የቤት ባለቤት እንዲሆን ቋምጦ እኮ ነው። ወይ ገርና አገሩ። እና ይኼ ወዳጄ ለበዓል መዋያ የያዘውን በጀት በቢራ ጨርሶት እኔን ካላበደርከኝ ‘ሞቼ እገኛለሁ’ ይለኛል። ለነገሩ አሁን አሁን በአገራችን ምርትን ለተጠቃሚዎች ማስተዋወቅ ደንበኞችን ለመሳብና ገቢን ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም፤ በአልኮል በተለይም በቢራ ምርቶች ላይ የሚታየው የማስተዋወቅ ሂደት ግን ወጣቱን ለሱስ የሚገፋፋ፤ ገቢን እንጂ ማህበራዊ ተጽዕኖውን ያላገናዘበ እንደሆነ ምሑራን ያስረዳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርትና ሥነ-ባህሪ ኮሌጅ ሥነ ልቦና ትምህርት ክፍል የማህበራዊ ሥነልቦና መምህር የሆኑት፣ ፕሮፌሰር ሃብታሙ ወንድሙ እንደሚናገሩት፤ የሰው ባህሪ የሚመሰርቱ ና ወደ ሱስ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ነገሮች ከእናትና አባት ከሚወረሱ ሁኔታዎች የሚጀምር ሲሆን፤ የአስተዳደግ ሁኔታና የግለሰቦች ውሎን ይመለከታል፡፡ በዚህም ሰዎች ምን ይሰራሉ፣ ምን ያያሉ፣ ከማን ጋር ይውላሉ፣ ምንስ ላይ ያተኩራሉ የሚሉ ጉዳዮች እና ሰዎች በለጋ ዕድሜ ላይ የሚኖራቸው መታለል፤ እንዲሁም የጓደኛ ብሎም የመገናኛ ብዙኃንና ሥራዎቻቸው ግፊት ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ለከት ያጣው የአልኮል በተለይም የቢራ ማስታወቂያና አጋዥ ገበያን የመሳቢያ መንገዶች ለወጣቶች በተለይም ለታዳጊዎች ወደ አልኮል ሱሰኝነት መግባት የበዛ ድርሻ አለው፡፡ የሰውየው ልጅ ይኼን ሰምቶ፣ ‹‹ለምን ጥቃቅንና አነስተኛ ሄደህ አትበደርም?›› አለው። ‹‹ቆርኪ አስይዤ?›› ብሎ አይመልስለት መሰላችሁ? ሆዴን ይዤ ክትክት አልኩ። ልሳቅ እንጂ ተውኝ። እንዴ አሮጌ ዓመት ሳያስተክዝ አያልፍም። የትካዜ ብዛት ደግሞ ሲያድግና ሲመነደግ ሆድ አስይዞ ያስቃል። ለዚያ አይመስላችሁም ከልማታዊ ፎቆቻችን ትይዩ አገራችን ኮሜዲያን በማፍራት ከዓለም አንደኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ የወጣችው። አልሰማችሁም እንዴ? ይህ አይነት አሉታዊ የቢራ ማስታወቂያ የጓደኛ ግፊት፣ የአከባቢያዊና የታላላቆች ተጽዕኖ፣ የሱስ አስያዥ ነገሮች ተደራሽነት እንዲሁም የመግዛት አቅም መፈጠር የሰው ልጆች ወደ ሱስ እንዲገቡ ከሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ምክንያቱም ሰዎች በተለይም ወጣቶች ከጓደኛ በሚደርስባቸው ተጽዕኖ ወይም ከቤተሰብና በጎልማሳነት የዕድሜ ደረጃ ካሉ ሰዎች ከሚመለከቱት ነገር ተነስተው እንደ አልኮል ዓይነት ለሱስ አጋላጭ የሆኑ ነገሮችን የመጠቀም ፍላጎታቸው ይጨምራል፡፡ የሚኖሩባቸው፣ የሚሰሩባቸው ወይም የሚማሩባቸው አካባቢዎች እንደ ጫትና አልኮል ከመሳሰሉ ነገሮች ጋር ያላቸው ቁርኝትም ለሱስ የሚጋለጡበትን ደረጃ ይወስናሉ በማለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ልቦና ምሑር  ዶክተር ትዕግስት ውሂብ ያብራራሉ። እናማ ዓይኔ ብዙ አየ። ዘመን መጣ ዘመን ሄደ። ሳወጣው ሳወርደው በዚህ አያያዜ ማንም ሰው ሳያውቀኝ ራሴን በራሴ እንዳቆለጳጰስኩ ጓደኛዬ ላይ ልደርስ ነው። ይህ ሲሆን ቆሜ አላይም ብዬ ለ2011 ዓ.ም. ቃል ገባሁ። በዚህ ዓመት ከእኔ በላይ የዝና ማማ ላይ የሚሰቀል መኖር የለበትም ብዬ ዕቅዴን ወደ ተግባር ለመለወጥ ስትራቴጂ መቀመር ጀመርኩ። ከልማታዊው መንግሥታችን በተማርኩት መሠረት ስትራቴጂ ሲቀመር ወደ ምሥራቅ መዞር ሊኖርብኝ ሆነ። ቻይናና ኮሪያ ደግሞ ጠንካራና አገራዊ እይታ ያለው የቀን ሠራተኛ እንጂ ስመጥር አያውቁም። ማለቴ ከአውራው ፓርቲያቸው በቀር ማለቴ ነው። ስለዚህ ኢኮኖሚያችን ከሚጓዝበት መስመር መማር አለብኝ ማለት ነው። ወደ ምዕራብ ዞርኩ። የምዕራባውያን ስመጥሮች እንኳን በአገራቸው፣ አገራችን መጥተው ብዙ እንደ ጎበኙን ትዝ አለኝ። ለነገሩ አሁን አሁንማ እየቀሩ ነው አሉ። ምክንያቱም በአለም ታዋቂ የሆንባቸው ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶቻችን በእኛ እንዝላልነት ፈራርሰዋል፤ ከጥቅም ውጭም ሆነዋል።  ለዚህም ነው ባለፈው እሁድ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር አብይ አህመድ በአማራ ክልል ከሚገኙት ቅርሶች መካከል ላሊበላ ውቅር ቤተክርስትያንን የጎበኙት።  በጉብኝታቸው ወቅት የተሰማቸውን ስሜት በመያዝ ከፈረንሳይ መንግስት ለቤተክርስትያኑ ዕድሳት ቀጥታዊ ዕርዳታ ሲገኝ ደግሞ ዕጅጉን ደስ አለን። ወደ ዋናው ሀሳቤ ስመለስ ዕድል በተሰጠኝ ቢራ ጠጥቶ ስመ ጥርነቴን የምቋቋምበት አቅም ሳላዳብር ደግሞ በኋላ ምን ልሆን ነው ብዬ ራሴን ስጠይቅ ‘አፍርሰህ ትሠራዋለሃ። በአገርህ እየሠሩ ሲያፈርሱ አይተህ አታውቅም?’ አለኝ ልቤ።  አሁን በምን ልታወቅ? ወደሚለው ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ስዞር ‘አፏጭ አፏጭ’ የሚል ድምፅ ሰማሁ። ብቻዬን ሆኜ ‘ማነው የት ነህ’ ስል ጓደኛዬ ቢያየኝ ሦስት ሰባት ያዝልኝ ነበር። ደግነቱ ብቻዬን ነኝ። አንዳንዴ ብቻ ሆኖ ማበድን የመሰለ ነገር የለም ። እናም በዚህ ገደብ ባጣው የቢራ ማሰታወቂያ የአልኮል መጠጦች ወጣቱጋ ያላቸው ተደራሽነት መጠጦቹን ለመሸጥ ከሚደረገው ሳቢ ማስታወቂያ ይጀምራል፡፡ ይሄም ወጣቶቹ የበለጠ የመሞከርና የመጠቀም ፍላጎታቸው እንዲነሳሳ ያደርጋቸዋል፡፡ ምክንያቱም አሁን በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ የአልኮል ፋብሪካዎች እየተስፋፉ ናቸው፤ ከፍተኛ የአልኮል መጠን ያላቸውና በውድ ዋጋ የሚገቡትም ተበራክተዋል፤ የአልኮል መገኛና መሸጫ ስፍራዎችም በየመንደሩ ዘልቀዋል፡፡ እነዚህ ደግሞ ለአዋቂ ብቻ ሳይሆን ለሕፃናት ስሜት ቅርብ ከሆኑ ማስታወቂያዎች፣ ከሽልማትና ስጦታዎች ጋር ተዳምረው መቅረብ ደግሞ ኅብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ የአልኮል ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎቱን ያሳድጉታል፡፡ ሕፃናት ሳይቀሩ የአፍ መፍቻቸው መዝሙር እስኪመስል የቢራ ማስታወቂያዎች በአዕምሯቸው ተቀርጸው የቢራ ስሞች በአፋቸው ላይ እንዲቀሩ አድርጓል፡፡ ይህም የቢራ ጠርሙሶቹ ጭምር የሚላበሱት አብረቅራቂና ሳቢ ቀለሞች ጋር ሲዳመር በሚያሳድረው ሥነልቦናዊ ጫና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ለነዚህ ቢራዎች ፍቅር እንዲኖራቸውና በመሞከር ጀምረው ወደሱስ እንዲገቡ የሚያደርግ ተግባር እንደሆነ ፕሮፌሰሩ በአጽኖት ይናገራሉ፡፡ ወደ ፉጨቴ ስመለስላችሁ ቀትር ሳልል ምሽት ‘ሰው መሆን አልቻልኩም ብርቄን ሰው ወድጄ’ እያልኩ ተያያዝኩት። ምነው በሰው ዘፈን እንዳትሉኝ ብቻ። ዋ ብያለሁ። ሰው በሰው ላብ ሰው በሚመስልበት በዚህ ጊዜ፣ ሰው በሰው ዜማ አቧራ በሚያስነሳበት በዚህ ወቅት፣ ታምኖ የተሾመ የሕዝብ ገንዘብ እየዘረፈ ለራሱም ለሚወዱትም ሳይሆን እንዳሴረ በሚቀርበት በዚህ ጊዜ እኔን እንዳታሙና ክፉ እንዳልናገር። ‹‹ባይሆን ይህን ወቅት አልፈን ታፏጫለህ። እስከዚያ ግን አይሆንም። እባብ ትጠራለህ፤›› ሲለኝ ክው አልኩ። ጓደኛዬ እኔ የማላውቀው ሕይወት አለው? ከመቼ ወዲህ ነው ባዕድ እምነት የጀመረው? ብዬ ትዝታዬን ስጠራጠር ነገሩ ገብቶት፣ ‹‹እባብ ስልህ ነገር ለማለት ነው። እስከ ዛሬ ነገር የጣለውን እንቁላል ሰብረን ሳንጨርስ ደግሞ አንተ አዲስ ልታስፈለፍልብን ነው?›› ብለው እንዳኮረፈኝ ወደ ቤቱ ተመልሶ ገባ። እኔም ምንም ቢሆን ከጓደኛዬ ቃል አልወጣምና ፉጨቴን ትቼ ጉዞዬን ቀጠልኩ። ስመ ጥር የመሆን ህልሜም በምሥራቅ ቢባል በምዕራብ ከሰመ። በሚነገረው የቢራ ማስታወቂያ መሰረትም ብዙ ብጠጣም ባስጠጣም ገንዘቤን ከመጨረስ ውጭ ምንም ጠብ የሚል ነገር የለም። እናውራው ብንል የእኛ ነገር አያልቅም። ‘አመለኛ ፈረስ ልጓም ያላምጣል’ ብለን እንለፈው እንጂ ብዙ ብዙ መከርከም ያለበት ነገር አለ። ልብ አልኖረኝ ብሎ ከጓደኛዬ ልጅ ጋር ትናንት አመሻሽ ላይ አንድ አንድ ልንል ወደ ግሮሰሪያችን እያመራን ሳለን፣ አንድ ከሰውነት ደረጃ የወረደ  ወጣት መጥቶ ፊታችን ወደቀ። ‹‹እናንሳው?›› ስለው የጓደኛዬን ልጅ፣ ‹‹ኧረ ተወው የት ታውቀዋለህ?›› አለኝ። ትተነው ወደ ግሮሰሪያችን ገባን። የግሮሰሪያችን ታዳሚ የዚያን ምስኪን መጨረሻ እርስ በርሱ ትከሻ ለትከሻ እየተንጠራራ ይከታተላል። አንዱ፣ ‹‹ይኼ ጫት ምናምኑ እኮ ነው እንዲህ የሚያደርገው...›› ይላል። ‹‹የለም ይኼማ የአዕምሮ በሽታ ነው። ቢታከም እኮ ይድናል። አካሚው ሳይጠፋ አሳካሚው ነው የጠፋው...›› ይላል። ‹‹የምን የአዕምሮ በሽታ ነው ደግሞ እሱ። ገና ለገና ዘመናዊ ነን ለማለት ሲሉ የሰሙትን መደጋገም አይደብራችሁም እንዴ? ይኼ አንድ ሁለት የሌለው የሰይጣን ሥራ ነው። ፀበል ቢሄድ በቃው። ተገላገለ...›› ይላል ወዲያ ማዶ ከጓደኛዬ ልጅ ጀርባ። ሌላው፣ ‹‹ተውት በአዲሱ አመት በአዲስ ተስፋ ይመለሳል...›› ይላል። እኔና የጓደኛዬ ልጅ ተያይተን ተሳሳቅን። አንዱ የአዕምሮ በሽታ ነው ሲል፣ አንዱ ሱሴ ነው ሲል፣ አንዱ ዘመን ነው ሲል የጋለ ንትርክ ተነስቶ አረፈ። የጓደኛዬ ልጅ፣ ‹‹ተመልከት የአስተሳሰብ ልዩነትና የግንዛቤ እጥረት። እንግዲህ ይኼ ሁሉ ሰው በየፊናው ትክክል ነኝ ካለ አይመለስም። ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው አገር የሚለወጠው? በተጨባጭ ማስረጃ መተማመን ዘበት በሆነበት ጎዳና ድክ ድክ ብለው የሚያድጉትስ እንዴት ብለህ ተስፋ ትጥልባቸዋለህ?›› ሲለኝ ቆም ብዬ አሰብኩ። ማሰብ ደጉ ሕይወትን ቢገራው እንዴት ሸጋ ነበር! እናም ምሑራኑ እንደሚናገሩት፤ የቢራ ማስታወቂያ ሂደቱ ገደብና ሥርዓት ያስፈልገዋል፡፡ ትውልዱን ከሱስ ድንዛዜ ለመታደግም ገበያን ለመሳብ በዚህ መልኩ የሚከናወኑ ተግባራት ኅብረተሰቡ ላይ የሚያሳድሩትን ሁለንተናዊ ጫና በመለየት በሚመለከታቸው ሁሉ ትኩረት ተሰጥቶ መስራትና በሕግ አግባብም አስፈላጊውን እርምጃና ማስተካከያ ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከወላጆች ጀምሮ፣ መንግሥትና ሚዲያው ጭምር መስራት አለበት፡፡ በትምህርት ቤቶች አካባቢም ግንዛቤ ማስጨበጥና በሱስ የተያዙትም ከሱስ የሚወጡበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የቢራ ድርጅቶችም ገቢን ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ጉዳቱንም ከግምት በማስገባት በጥናት የተደገፈ የማስተዋወቅ ሥራ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለአብነት ያክል የቢራን ማስታወቂያ መዘዝን አነሳሁ እንጂ ሌሎች አገራዊም ሆኑ ከውጭ አገር የመጡ ምርቶች ከሚሰጧቸው አገልግሎቶችና ይዘታቸው በላይ ማስታወቂያቸው ብቻ ጎልቶ እንደሚታይ በየጊዜው የሚወጡ ሪፖርቶች ያስረዳሉ። ስለሆነም ይህን ገደብ የዘለለውን የማስታወቂያ ተግባር በወቅቱና በህጉ ማስተካከል ካልተቻለ  ወጣቱ ጊዜያዊ ደስታን ፍለጋ መጠጥን ደጋግሞ በመውሰድ ለሱስ ይጋለጣል፤ በሱስ ተጠምዶ የሚውል ትውልድን በመፍጠርም ለሥራ የተዘጋጁ እጆች ሥራ ላይ ከመዋል ይልቅ ያላቸውን ገንዘብ ለሱስ ማስታገሻ እንዲያውሉ፣ ከዚያም አልፈው ለልመና ጭምር እንዲሰማሩ፣ ሱስን ተከትለው ለሚመጡ የጤና ችግሮችና ሌሎች ማህበራዊ ቀውሶች የሚዳረጉበት ሰፊ ዕድል ይፈጠራል፡፡ በትምህርትና በሥራ ላይ መዋል የሚገባው ኃይልም በሱስ ተጠምዶ ለመዋል፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሱም እያደገ እንዳይሄድ የሁሉም ዜጋ ጥረት ይፈልጋል፡፡ ቸር እንሰንብት!    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም