ለትምህርት ፍኖተ ካርታ ግብአት ለማሰባሰብ አገር አቀፍ ውይይት እየተካሄደ ነው

47
አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2011 ለትምህርት ፍኖተ ካርታ ግብአት ማሰባሰብን ያለመ አገር አቀፍ ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። ውይይቱ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ የሀይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ናቸው። በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትምህር ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላየ ጌቴ እንደሉት፤ አገሮች ለሳይንስና ምርምር እንዲሁም ስልጠና የሚሰጡት ትኩረት በኢኮኖሚ ልማታቸው ላይ ቁልፍ ሚና አለው። በኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በላይ እየተተገበረ ያለው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በአገሪቱ ለተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ እድገት የራሱን ሚና መጫወቱን አስታውሰዋል። ፖሊሲውን አሁን አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታና ግብ ጋር ማጣጣም በማስፈለጉ አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በውይይቱ የሚገኘው ግብአትም በፍኖተ ካርታው ወጤታማነት ላይ  የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል። በውይይቱ በኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው የቡድን ውይይት እንደሚካሄድ በመርሐ ግብሩ ተመልክቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም