ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ - ኢዜአ አማርኛ
ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2011 ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ። ዛሬ በተካሄደው 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 4ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሹመት ጸድቋል። ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ፍርድ ቤቱን በፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ዳኜ መላኩን በመተካት ነው። አቶ ዳኜ መላኩ አሁን ያለውን ለውጥ ለማስቀጠልና ፍርድ ቤቱ በሙሉ አቅሙ ህዝብ የሚጠብቀውን ፍትህ መስጠት የሚችልና የተሻለ አቅም ያለው ሰው ካለ በገዛ ፍቃዳቸው ቦታቸውን ለመልቀቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ምክር ቤቱ አዲስ ፕሬዝዳንት ሾሟል። ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የትውልድ ቦታቸው አሶሳ ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ትምህረት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከአሜሪካ ኬንታኪ ዩኒቨርሲቲ በዓለም ዓቀፍ ግንኙነት የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው የህግ ባለሙያ፣ ዳኛ እና በህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ ያገለገሉ ናቸው። በሰብዓዊ መብት የሴቶችና ህጻናት መብቶች እንዲካተቱ ከሌሎች ጋር ሰፊ ጥረት ያደረጉ፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለህጻናትና ለሴቶች መብት መከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱና የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር እንዲመሰረት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ መሆናቸውም እንዲሁ። ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ድርጅትን በዳይሬክተርነት የመሩ ከመሆናቸውም ባሻገር ለተጎዱ ሴቶች በነጻ ጥብቅና የሚቆሙ ተቆርቋሪ እንስት ናቸው። በአሁኑ ወቅትም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ዳኜ መላኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም መሆኑ የሚታወስ ነው።