የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሹመትን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል

አዲስአበባ ጥቅምት 22/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሹመትን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ይካሄዳል። በስብሰባው በህገ መንግስቱ አንቀጽ 81 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቡትን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እጩ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ሹመት መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅት ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ያሉት አቶ ዳኜ መላኩ እና አቶ ጸጋዬ አስማማው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም ነበር። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ መላኩ በ1980 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ አግኝተዋል። በአዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በረዳት ዳኝነትና በዳኝነት እንዲሁም በአዲስ አበባ የዞን ፍርድ ቤት እና በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከየካቲት 30 ቀን 1992 ዓ.ም ጀምሮ 2008 ዓ.ም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው አገልግለዋል። የ55 ዓመቱ የህግ ባለሙያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ ወር 2008 ዓ.ም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በመሆን የተሾሙት አቶ ዳኜ መላኩ ላለፉት ሁለት አመታት ከመንፈቅ ያህል በዚህ ሀላፊነት ቆይተዋል። አቶ ዳኜ በአጠቃላይ ለሶስት አስርት ዓመታት የሚጠጋ ጊዜ በዳኝነት በማገልገል የረጅም ጊዜ ልምድ አላቸው። አቶ ዳኜ የጠቅላይ ፕሬዚዳንትነት ስራውን የተረከቡት የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንትነታቸውን በገዛ ፍቃዳቸው በለቀቁት አቶ ተገኔ ጌታነህ ምትክ ነበር። የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጸጋዬ አስማማው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1986 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ከ1987 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ በመቀሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እንዲሁም የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን አገልግለዋል። አቶ ጸጋዬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንዲሁም የአዲስ አበባ ምርጫ ቦርድ ቢሮ ኃላፊ በመሆንም ሰርተዋል። ወደ ትግራይ ክልል በመመለስም የክልሉ የጸጥታና አስተዳደር ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ እና የርዕሰ መስተዳድሩ የሕግ አማካሪም ነበሩ። በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን አቶ ጸጋዬ መላኩ ላለፉት ሁለት አመታት ከመንፈቅ ያህል በጠቅላይ ፍርድ ቤት በምክትል ፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል። አቶ ጸጋዬ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ስራውን የተረከቡት ከአቶ መድኅን ኪሮስ ነበር።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም