በአዲስ አበባ ህገ-ወጥ እርድና የስጋ ዝውውርን ለመቆጣጠር ዘመቻ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህገ-ወጥ እርድንና የስጋ ዝውውርን ለመቆጣጠር ተከታታይ ዘመቻ እንደሚያካሂድ አስታወቀ። የመዲናዋ ንግድ ቢሮ ህገ-ወጥ እርድና የሥጋ ዝውውርን ለመቆጣጠር ባለፈው ዓመት የወጣውን ደንብ ተግባራዊ እንደሚያደረግም ገልጿል። በቢሮው የከተማ ግብርና ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ በሰጡት መግለጫ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ህገ-ወጥ እርድና የስጋ ዝውውር ተግባር በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል። በህገ-ወጥ መንገድ ለገበያ የሚቀርበው ሥጋ እየተባባሰ በመምጣቱ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚገኙ ቄራዎች የሚያቀርቡት ሥጋ በተለይ የፍየልና የበግ  ከሚጠበቅባቸው መጠን በታች እንዲሆን አደርጎታል ብለዋል። በህገ-ወጥ መንገድ ታርዶ የሚቀርበው ሥጋ በኀብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መሆኑንም አቶ አሰግደው ገልጸዋል። በተለይ ቅድመና ድህረ እርድ ምርመራ ሳይደረግ፣ ንጽህናው የተጓደለ፣ ከህግና ከሰው እይታ በመሰወር በከተማዋ ቆሻሻ ቦታዎችና በሆቴሎች ጀርባ የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ እርዶች በኀብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር እያደረሰ መሆኑን አስረድተዋል። ህገ-ወጥ ድርጊቱ በመንግስት ገቢ፣ በፍትሃዊ የንግድ ውድድርና የአካባቢ ብክለት ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን አመልክተዋል። ችግሩን ለመፍታት ህጋዊ አሰራር ያልነበረ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው በአሁኑ ወቅት ግን ቁጥጥር ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። ማናኛውም እርድ በቄራዎች ብቻ እንዲከናወን እንዲሁም የከብት ስጋ ህጋዊ ፍቃድ ባላቸው የስጋ ማጓጓዣ ተሽከረካሪዎች ብቻ  እንዲያጓጉዝ ህጝ የተደነገገ መሆኑን አመልክተዋል። ሁሉም ሉኳንዳ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ ባርና ሬስቶራንቶች እንዲሁም የፍየል ስጋ መሸጫ ቤቶች በቄራ የታረደ ከብት ብቻ እንዲጠቀሙ አቶ አሰግድ አሳስበዋል። ስጋው በቄራ የታረደ መሆኑን የሚያረጋግጥ የምርመራ ማህተም የተመታበት ማስረጃ ይዘው መገኘት አለባቸው ያሉት ኃላፊው ከቄራ ውጭ የታረደ ስጋ ይዞ የተገኘ አካል ተጠያቂ እንደሚሆን ተናግረዋል። አቶ አሰግደው እንደገለጹት ህጉን የሚተላለፉ አካላት ከብር 7 ሺህ እስከ 10 ሺህ ቅጣትና ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወር የሚደርስ እስራት ይጠብቃቸዋል። በተጨማሪም የተገኘባቸው ህገ-ወጥ ስጋ ተወርሶ እንዲወገድ ይደረጋል ብለዋል። በከተማዋ ህገ-ወጥ እርድና የስጋ አቅርቦት ላይ በተሰማሩ ሉኳንዳ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች፣ ባርና ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች ላይ ተከታታይ የሆነ ዘመቻ እንደሚካሄድ ገልጸዋል። የመዲናዋ ነዋሪዎችም በሚደረገው ቁጥጥር እንዲተባበርና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተመለከተ ጥቆማ እንዲሰጥ አቶ አሰግድ ጥሪ አቅርበዋል። በከተማዋ ተግባራዊ የሚደረገው የህገ -ወጥ እርድና ስጋ ዝውውር ለመከላከል የወጣው ደንብ ለንግድ በሚቀርብ ስጋ ላይ እንጂ ለመኖሪያ ቤት ፍጆታ የሚፈጸምን እርድ አያካትትም ብለዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ሦስት ቄራዎችና ከእምስት ሺህ በላይ ሉኳንዳ ቤቶች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም