የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የግል ድርጅቶች ማእከል በአዲስ አበባ ክፍለ አህጉራዊ ቢሮ ከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የግል ድርጅቶች ማእከል በአዲስ አበባ ክፍለ አህጉራዊ ቢሮ ከፈተ
አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2/2011 የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የግል ድርጅቶች ማእከል በአዲስ አበባ ክፍለ አህጉራዊ ቢሮ ከፈተ። የቢሮው ተልእኮ በዴሞክራሲ እና በግሉ የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴ መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን ማለሙን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሚስተር ሚካኤል ሬይኖር ፖለቲካዊና ምጣኔ ኃብታዊ ነጻነት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ጠቅሰው የማዕከሉ ራዕይ የግሉን ሴክተር እንቅስቃሴ፣ እኩል ተጠቃሚነትና ዲሞክራሲን ማጎልበት ነው ብለዋል። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የተሟላ ምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካዊ እድሎችን ለመፍጠር ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማገዝ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለውም አክለዋል። ማዕከሉ በዓለም ላይ ዴሞክራሲን ለማስፋፋት በሚል የተቋቋመውና በአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው መንግስታዊ ያልሆነው "ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዲሞክራሲ" የተሰኘ ተቋም አካል ነው። የማዕከሉ ተልዕኮ የሚያተኩረው የንግድ ተቋማት ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ የዲሞክራሲ ተቋማት ምቹ አካባቢን በመፍጠሩ በኩል ያላቸውን ጠቀሜታ ማጎልበት ላይ ነው። ለንግድ ተቋማት ምቹ ሁኔታ መፍጠር የስራ ፈጠራን ለማጠናከር፣ ትርጉም ያለው የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር፣ ለሰራተኞች የስልጠናና የአቅም ግንባታና ፍትሃዊ የሰራተኞች አያያዝን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል። የንግድ ተቋማትና የሕብረተሰቡ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖርም ያስችላሉ ብለዋል። ባለፈው ዓመት ነሀሴ ወር በማዕከሉና በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መካከል የጋራ የትብብር መግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈርሟል። ስምምነቱ ሁለቱ አካላት ምጣኔ ኃብታዊና ዲሞክራሲያዊ ለውጦችን ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ሲሉ አምባሳደሩ ተናግረዋል። ማዕከሉ የተከፈተው በኢትዮጵያ የስራ እድል ፍላጎትና ምጣኔ ኃብታዊ ጥያቄዎች ከምንግዜውም በላይ በጨመረበት ወቅት በመሆኑ ትክክለኛ ጊዜ መሆኑን አንስተው ከማዕከሉ ብዙ ስራዎች እንደሚጠብቁም ጠቁመዋል። ማዕከሉ እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ስራዎችን ለማጠናከር ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው በአዲስ አበባ ቢሮ መከፈቱ ይህንን ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል። የንግድ ዘርፍ ማህበራት የስራ እድል ለመፍጠር ቀጣይነት ያለውና ማህበራዊ ሀላፊነትን ለመወጣት ጉልህ ሚና ያላቸው በመሆኑ ይህ ድጋፍ ይቀጥላል ብለዋል። ማዕከሉ የንግድ ዘረፍ ማህበራትንና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን በመደገፍ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ቀጣይነት ካለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ብልጽግና እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን እገዛ የሚያደርግ መሆኑንም አክለዋል።