አምባሳደር ዶክተር ሽፈራዉ ተክለማርያም በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራዉ ተክለማርያም በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት አደረጉ
አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ሽፈራዉ ተክለማርያም በአገሪቱ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ትናንት ውይይት አደረጉ። ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በደቡበ አፍሪካ የሚኖሩ የተለያዩ አገራት ዜጎች የተለያየ ጥቃት እንደሚፈፀምባቸው ሲገለፅ ይሰማል። አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር ያደረጉት ውይይት ኢትዮጵያዊያኑ በአገሪቱ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች መብትና ግዴታዎቻቸውን አውቀው ህይወታቸውን በሰላም መግፋት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። ኢትዮያዊያኑ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው በኤምባሲው በኩል የሚደረጉ ድጋፎችን በተመለከተም ውይይት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በአካባቢው የሚገኙ የኢትዮጵያውያን አደረጃጀቶችን በማጠናከር የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በመረዳዳት እና በትብብር መንፈስ ለመፍታት እንዲጥሩም ጥሪ ቀርቧል። ኢትዮጵያዊያኑ ከደቡብ አፍሪካውያን ጋር ያላቸውን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ማጠናከርም የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። የማህበረሰቡን አንድነት የሚፈታተን ሁኔታ ሲፈጠርና የወንጀል ጥቃት ሲያጋጥም ለአገሪቱ የፀጥታ አካላት ፈጥኖ ከማሳወቅ ጎን ለጎን ከኤምባሲው ጋርም ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ተመልክቷል። ኢትዮጵያውያኑም በበኩላቸዉ በደቡብ አፍሪካ ሲኖሩ የአገሪቱን ህግና ስርአት አክብረዉ በመንቀሳቀስና አንድነታቸዉን በማጠናከር የሚያጋጥሙ ችግሮችን በወንድማማችነት መንፈስ ለመፍታት ቃል ገብተዋል። አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁለ-ገብ የለውጥ እንቅስቃሴ በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል። ኢትዮጵያዊያኑ በአገራቸው ልማት በመሳተፍ ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው ጉዳዮች ላይም አምባሳደሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።