ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የለውጥ እርምጃ ለአፍሪካ አህጉር ምሳሌ የሚሆን ነው - የፍራንክፈርት ምክትል ከንቲባ ኡው ቤከር

አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 "በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የለውጥ እርምጃ ለመላው የአፍሪካ አህጉር ምሳሌ የሚሆን ነው" ሲሉ የፍራንክፈርት ምክትል ከንቲባ ኡው ቤከር ገለጹ። በአውሮፓ የሚኖሩ ከ20 ሺህ የሚልቁ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በጀርመን ፍራንክፈርት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በኮሜርዝባንክ አሬና ስታዲየም እየተካሄደ ባለው በዚሁ አቀባበል ላይ የፍራንክፈርት ከተማ ምክትል ከንቲባ ኡው ቤከር ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር "በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የለውጥ እርምጃዎች ለአገሪቷ ህዝብ ተስፋ የሰጠና የወደፊቱ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሩህ እንደሚሆን አመላካች ነው" ብለዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የወሰዷቸው የማሻሻያ እርምጃዎች በተለይም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም እንዲሰፍን ላደረጉት ጥረትና ግማሽ የካቢኔው አባላት ሴቶች እንዲሆኑ ማድረጋቸውን አድንቀዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ አጠቃላይ ማሻሻያዎች ለአፍሪካ አህጉር ምሳሌና ለአህጉሪቷ ተስፋን የሚሰጥ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት አፍሪካ ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩባትም በዛው ልክ ተስፋን የሚፈነጥቁ ነገሮች መኖራቸውን ያመለከቱት የፍራንክፈርት ከተማ ምክትል ከንቲባ "እርምጃዎቹ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ አይቶት የማያውቀውን ተስፋ የሰጠ ነው" ብለዋል። ዶክተር አብይ 'ኢትዮጵያን በጋራ በመስራት ነገን እንገንባ' በሚል ለኢትዮጵያ ህዝብና ዳያስፖራ ያቀረቡትን ጥሪ አድንቀዋል። ይህም በህዝቡ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በህዝቡ ላይ የፈጠሩት ይህ እምነት እና በአገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት እያደረጉት ያለው ጥረት ለአፍሪካ ጭምር ብሩህ ተስፋ የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል። በፍራንክፈርት የሚገኙ የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ እንዲያፈሱና ለውጡን እንዲደግፉ ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል። በፍራንክፈርትና በሌሎች የጀርመን ከተሞች የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችንም "በጣም አስደናቂ ናቸው" ሲሉ ገልጸዋቸዋል። ፍራንክፈርት ብዙ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ባህሎች ያሏቸው የተለያዩ ህዝቦችን አቅፋ እንደምትኖርና ይህ የሚያሳየው በብዝሃነት መኖር ለማህበራዊ ኑሮ ብሩህ ቀለምና ድምቀት የሚፈጥር ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይህ የፍራንክፈርት ጉብኝት የመጨረሻው እንደማይሆንና ተጨማሪ ጉብኝት በማድረግ ከፍራንክፈርት- አዲስ አበባ ከጀርመን እስከ ኢትዮጵያ ድልድይ እንገንባ  ሲሉም ገልፀዋል ምክትል ከንቲባ ኡው ቤከር።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም