ቀጥታ፡

የማህበራዊ የጤና መድህን አዋጅ ከወጣ ስምንት ዓመት ቢያልፈውም እስከ አሁን ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም

አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 በኢትዮጵያ ተቀጥሮ የሚተዳደረውን ሰራተኛ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ በ2002 ዓ.ም የወጣው የማህበራዊ ጤና መድህን አዋጅ እስከ አሁን ድረስ ተግባራዊ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ አስታወቀ። አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ ያልተቻለው ሰራተኛው በአዋጁ በተደነገጉ ጉዳዮች ላይ የተለያየ ጥያቄ በማንሳቱ እንደሆነም ገልጿል። በ2003 ዓ.ም የተቋቋመው የጤና መድህን ኤጀንሲ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ በማህበራዊ የጤና መድህን መርሃ ግብር የሚታቀፉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ከኢኮኖሚ፣ ከጤና አገልግሎት ሽፋንና አተገባበር ዙሪያ በርካታ ጥያቄዎች በማንሳታቸው እንደሆነም ጠቁሟል። የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አታክልቲ አብርሃ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሰራተኞች ከደመወዛቸው ሦስት በመቶ መዋጮ እንዲያደርጉ እንዲሁም ባልና ሚስት ተቀጣሪ ከሆኑ ሁለቱም መዋጮ ያደርጋሉ የሚለው የአዋጁ ድንጋጌ ተቃውሞ ገጥሞታል። አዋጁን ለመተግበር የሚደግፍ ደንብና መመሪያ ወጥቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አታክልቲ በሰራተኛው ዘንድ ተቃውሞ በማስነሳቱ ወደ ተግባር መግባት እንዳልተቻለ ተናግረዋል። የማህበራዊ የጤና መድህን ወደ ተግባር ባይሸጋገርም መደበኛ ባልሆነ የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኘው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ስኬታማ እንደሆነ ጠቁመዋል። የማህበራዊ የጤና መድህን አዋጅ ላይ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚያስችል መልኩ አዋጁ ዳግም በማሻሻል እንዲወጣ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አቶ አታክልቲ ተናግረዋል። አዋጁ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። የማህበራዊ የጤና መድህንን ለመተግበር በሰራተኛው ዘንድ ከዚህ በፊት ይነሳ የነበረው ተቃውሞ በአሁኑ ወቅት ተቀይሮ እንዲተገበር ጥያቄ እየቀረበ መምጣቱን ጠቁመዋል። ማህበራዊ የጤና መድህን ተግባራዊነት የተጓተተው ከሰራተኛው በቀረበ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ተቋሙ አዲስ በመሆኑ የማደራጀት ስራው እስኪጠናቀቅ ጭምር እንደሆነም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት አዋጁ ተሻሽሎ ቢወጣ ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስችል ተቋማዊ ቁመና መኖሩንም ጠቁመዋል። የጤና መድህን ስርዓት ለኢትዮጵያ አዲስ ስርዓት ሲሆን ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን በ2003 ዓ.ም በአራት ክልሎች በሚገኙ 13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ በአሁኑ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም