ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ ያደረግንበት ቦንድ አልተሰጠንም - የአርባ ምንጭ ከተማ መምህራን - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ ያደረግንበት ቦንድ አልተሰጠንም - የአርባ ምንጭ ከተማ መምህራን
አርባምንጭ ጥቅምት 21/2011 የአርባ ምንጭ ከተማ መምህራን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ከወር ደመወዛቸው ድጋፍ ያደረጉበት ቦንድ አልተሰጠንም ሲሉ ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት በበኩሉ የመምህራኑ ቅሬታ ተገቢ በመሆኑ በተያዘው ሳምንት ምላሸ እንደሚሰጥ አመልክቷል፡፡ በአርባ ምንጭ የኩልፎ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አንዱአለም ኃይለሚካኤል ለኢዜአ እንዳሉት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ከየካቲት 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በዓመት ውስጥ ክፍያውን ቢጠናቅቁም ቦንድ እንዳልተሰጣቸውና ገንዘቡም የት እንደገባም ምላሽ አለመሰጠቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡ ከወር በፊት በትምህርት ፍኖተ ካርታ ውይይት ወቅት ጥያቄውን አንሰተው 38 ሚሊዮን ብር የመምህራን ገንዘብ ባንክ ገቢ መደረጉንና ቦንዱ ይሰጣችኋል ተብለው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ምላሽ ባለመሰጠቱ ጉዳዩን ለአርባ ምንጭ ከተማ ፣ ለጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደርና ትምህርት ተቋማት በጽሑፍና በአካል ማሳወቃቸውን አስረድተዋል፡፡ የሚመለከተው አካል ገንዘባቸው ያለበትን እስኪያሳውቃቸውና ቦንድ በመስጠት መብታቸውን እስኪከበር ድረስ ስራ እስከማቆም ተቃውሟቸውን እየገለጹ መሆናቸውን አስረድተዋል። "ለህዳሴው ግድብ አሻራችንን ለማሳረፍ ያደረግነው በጎ አስተዋጽኦ ቢሆንም በመንግስት አካላት የአሠራር ግልጸኝነት አለመኖሩ አስቆጥቶናል" ያሉት የሲቀላ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሠረታዊ መምህራን ማህበር ተወካይ መምህር ፀሐዬ ጦና ናቸው ፡፡ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል የወር ደመወዛቸውን ለከፈሉበት ቦንድ እንዲሰጣቸው ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ምላሽ ባለማግኘታቸው ቅር መሰኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ የዚሁ ትምህርት ቤት መምህርት ገነት ወርቁ በበኩላቸው ለግድቡ ግንባታ የወር ደመወዛቸውን ድጋፍ ላደረጉበት ቦንድ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ቦንዱ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ላቀረቡት ጥያቁ ምላሽ ባለማግኘታቸው ስራ እስከማቆም መቃወማቸውን አመልክተው "በዚህም ምክንያት ተማሪዎቻችን እየተጎዱብን ነው፤ ለዚሁ ደግሞ ትምህርት ጽህፈት ቤቱ ተጠያቂ መሆን አለበት" ብለዋል፡፡ አፋጣኝ ምላሽ ተሰጥቷቸው የእረፍት ቀናትን በመጠቀም የባከነው ክፍለ ጊዜ ለማካካስ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የአርባ ምንጭ ከተማ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አቶ ሰብስቤ ቡናቤ ስለጉዳዩ ተጠይቀው የመምህራን ቅሬታ ተገቢ መሆኑና ምላሹም በተያዘው ሳምንት ውስጥ እንደሚሰጥ ገልጸዋል ፡፡ መምህራኑ የወር ደመወዝ ቆርጠው እንደጨረሱ ቦንድ ማግኘት ሲገባቸው የአርባ ምንጭ ከተማ ፋይናንስ ጽህፈት ቤት ገንዘቡን በጊዜ ባንክ ባለማስገባቱ የተነሳ መዘግየቱን አስረድተዋል ፡፡ በከተማዋ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶን ጨምሮ 38 ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ያመለከቱት ኃላፊው ከእነዚህ ውስጥ ስራ ያቆሙት የ11 ትምህርት ቤቶች መምህራን እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡ መምህራኑ ለጥያቄያቸው ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ ወደ መደበኛ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል ፡፡