ጠንካራ የስራ ባህልንና ሃገር መገንባትን ከአውሮፓውያን ልንማር ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
ጠንካራ የስራ ባህልንና ሃገር መገንባትን ከአውሮፓውያን ልንማር ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
ጥቅምት 21/2011 በአንደኛውና በሁለተኛው የአለም ጦርነት ደቀው የነበሩት አውሮፓውያን በጠንካራ የስራ ባህልና ተስፋ ባለመቁረጥ ሃገራቸውን መገንባታቸው ለኢትዮጵያውያን ትምህርት ሊሆን እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጀርመን ፍራንክፈርት ተገኝተው በአውሮፓ የሚኖሩ ከ20 ሺህ ለሚልቁ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ንግግር አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያውን ልክ እንደ አውሮፓውያን በጦርነት ውስጥ በማለፍ ተመሳስሎ አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ፍራንክፈርት በሁለተኛው የአለም ጦርነት ተጎድታለች፣የማይበገሩት ፍራንክፈርቶች ግን በ40 አመት ውስጥ ግንብተዋታል ይህ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ትምህርት ነው” ብለዋል፡፡ ጀርመኖች ለጦርነት ዳርጓቸው የነበረው “የኔ ዘር ይበልጣል እና የበላይነት አስተሳሰብ ድህነት፣ጉስቁልና፣ ወረርሽና እልቂት እንዳስከተለባቸው በመረዳት የልዩነት ግንብን በማስወገድ በመላው አለም ሚሊዮኖችን እንዳስጠለሉ ዶክተር አብይ ተናግረዋል፡፡ ጀርመኖች ወገባቸውን አስረው ተስፋ መቁረጥን አስወግደው አንድ ሆነው ስለሰሩ ለስኬት መብቃታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሃገራችን በኢኮኖሚ እንድትበለፅግና በፖለቲካ እንዲሳካላት አሁን በእጃችን ያሉትን ነፃነትና ተስፋ ተጠቅመን በተባበረ ክንድ ታላቋን ኢትዮጵያ መፍጠር እንችላለን ነው ያሉት፡፡ “የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል በመሳሪያና በአመፅ የታጀበ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ያለው የለውጥ ጉዞ ያላየነውን የምናይበት ጊዜ በመሆኑ በተባበረ ክንድ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ “ጌዜያችንን የማይጠቅም ነገር ላይ አናሳልፍ ፣በማንቀይረው ትናትና ላይና በሌሎች አጀንዳም አንጠመድ፣ጌዜውን መጣያ እንዳጣ ሰውም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ብቻ አናሳልፍ” በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡