በያቤሎ ወረዳ የተጀመረው የገጠር መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው

143
ነገሌ ጥቅምት 21/2011 በቦረና ዞን ያቤሎ ወረዳ በ13 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመረው የገጠር መንገድ ግንባታ 65 በመቶ መጠናቀቁን የወረዳው መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ። የወረዳው ነዋሪዎች በበኩላቸው የመንገድ ችግራቸው እንዲፈታላቸው ለዓመታት ሲያቀርቡት የነበረው ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ገልፀዋል። በባለስልጣኑ የመንገድ ሥራ ባለሙያ አቶ ዳፌ ፀጋዬ እንደሉት በያቤሎ ወረዳ ኩበኩቤ ካቴቡ የገጠር ቀበሌ እስከ ያቤሎ ከተማ 28 ኪሎ ሜትር ሁለተኛ ደረጃ የጠጠር መንገድ ግንባታ ሥራ በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም መጀመሩን ገልጸዋል። የመንገድ ግንባታ ሥራው በታቀደለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው እስካሁን በተሰራው ሥራ የ18 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ሥራ መጠናቀቁንና መንገዱም በከፊል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። የመንገድ የህብረተሰቡ አንገብጋቢ ችግር መሆኑ፣ ቀልጣፋ የፋይናንስ አገልግሎት መኖሩና የሥራ ተቋራጩ የሥራ ተነሳሽነት ሥራው በታቀደለት የጊዜ ገደብ እንዲከናወን አስተዋጾ ማድረጉን አስረድተዋል። በያቤሎ ወረዳ የተጀመረው የጠጠር መንገድ ግንባታ ሥራ ለአርብቶ አደሩ በበጋና በክረምት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ዳፌ ገልጸዋል። "አዲስ እየተሰራ ያለው መንገድ ሲጠናቀቅ የኩበኩቤ ካቴቡንና የጅጀግዱ ቀበሌዎችን ከያቤሎ ከተማ ጋር በማገናኘት ከ60 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል" ብለዋል። አቶ ዳፌ እንዳሉት የመንገዱ ግንባታ ሥራ ሙሉ ለሙሉ እየተከናወነ ያለው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መንገዶች ባለስልጣን በተመደበ 13 ሚሊዮን ብር ነው። የመንገድ ግንባታ ሥራው ከአንድ ወር በኋላ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ከስራ ተቋራጩ ጋር ስምምነት ላይ  ተደርሶ እየተሰራ መሆኑንም አምልክተዋል። በአቤሎ ወረዳ የኩበኩቤ ካቴቡ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቦሩ ጀልደሳ የበርካታ ዓመታት የመንገድ ጥያቄያቸው ምላሽ በማግኘቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። ከእዚህ ቀደም በአካባቢያቸው በነበረ የመንገድ ችግር የታመሙና በምጥ የተያዙ እናቶችን በበቅሎና በቃሬዛ በማጓጓዝ ወደ ጤና ተቋም ወስደው ያሳክሙ እንደነበር አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት የመንገዱ መሰራት የግር ጎዞ ድካምን ከማስቀረት ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በማፋጠን የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገው አመልክተዋል። በእዚሁ ወረዳ የጀጀግድ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኪያቶ ጫጩ  በበኩላቸው የመንገዱ መሰራት ቀደም ሲል ከተማ ደርሶ ለመመለስ ቀን ሙሉ ይወስድ የነበረውን የእግር ጉዞና ድካም ይቀንሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። እንስሳትና የግብርና ምርቶቻቸውን ለመሸጥ ወደያቤሎ ከተማ ገበያ ሲሄዱ በመንገድ እጦት ምክንያት አንድ ቀን ማደርና አላስፈላጊ ወጪ ማውጣት ግድ እንደሚል ያስታወሱት አቶ ኪያቶ፣ አሁን እየተገነባ ያለው መንገድ ይህን ችግራቸውን ስለሚያቃልል መደሰታቸውን ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም