ለኢትዮጵያ ወንዶች ከ23 ዓመት በታች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ጥሪ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ወንዶች ከ23 ዓመት በታች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ጥሪ ተደረገ
አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድር ማጣሪያ ለተመረጡ 26 ተጫዋቾች ጥሪ ተደረገ። የኢትዮጵያ ወንዶች ከ23 ዓመት በታች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ውድድሩን ከሶማሊያ አቻው ጋር ያደርጋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በህዳር ወር 2011 ዓ.ም ለሚደረገው ጨዋታ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግና ከፍተኛ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን እንደመረጡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ከተጠሩት ተጫዋቾች መካከል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፍሬዘር ካሳና አቡበከር ሳኒ ከኢትዮጵያ ቡና አቡበከር ነስሩና ሚኪያስ መኮንን፣ ከኢትዮ ኤሌትሪክ በሃይሉ ተሻገር፣ ከአርባ ምንጭ ከተማ ግብ ጠባቂው ፅዮን መርድና ከደደቢት አቤል እንዳለ በዋነኛነት ይጠቀሳሉ። ከሃዋሳ ከተማ መሳይ ጳውሎስ፣ ከፋሲል ከተማ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ደስታ ደሙ፣ ከመከላከያ ቴድሮስ ታፈሰ፣ ከባህርዳር ከተማ ወንድሜነህ ደረጀ፣ ከወላይታ ድቻ በረከት ወልዴና ከሽሬ እንደስላሴ ሸዊት ዮሐንስ በብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ የቀረበላቸው ናቸው። ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ነገ ከቀኑ 9 ሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ፌዴሬሽኑ ጥሪውን አስተላልፏል። የኢትዮጵያ ወንዶች ከ23 ዓመት በታች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ህዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም ከሶማሊያ አቻው ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን በሶማሊያ ያለው ጸጥታ አስተማማኝ ባለመሆኑ የመልስ ጨዋታው ከህዳር 9 እስከ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ በጅቡቲ እንደሚካሄድ እየተገለጸ ይገኛል።