ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ እኩለ ቀን በፍራንክፈርት ከኢትዮጵያዊያን ጋር ይወያያሉ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ እኩለ ቀን በፍራንክፈርት ከኢትዮጵያዊያን ጋር ይወያያሉ

አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ እኩለ ቀን በአውሮፓ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ጋር በጀርመን ፍራንክፈርት ይወያያሉ። ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ጀርመን የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በአንድነት እንነሳ፣ ነገንም እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር ውይይቱን የሚያካሄዱት። በዚሁ ኮሜርዝባንክ አሬና ስታዲየም በሚካሄደው ውይይት ላይ ከመላው አውሮፓ የተወጣጡ ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ይታደማሉ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳለው ውይይቱ ኢትዮጵያን በጋራ መገንባትና መንግስትም ዳያስፖራዎችን መደገፍ በሚችልበት መንገድ ላይ ያተኮራል። በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በሚቋቋምበት መንገድ መነጋገርም ከአጀንዳዎቹ መካከል አንዱ ነው ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ከጀርመን መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርከልና ከኦስትሪያ መራሂ-መንግስት ሰባስቲያን ኩርዝን ጋር ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦስትሪያ መራሂ-መንግስት ሰባስቲያን ኩርዝ ጋር ባካሄዱት ውይይት በሁለቱ አገሮች የጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። የአገሮቹን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስም በመሪዎች ደረጃ ጉብኝት ለማድረግም ተስማምተዋል። ከዚህም ሌላ ዶክተር አብይ ከዓለም ባንከ ፕሬዝዳንት ጂም ዮንግ ኪም ጋር ተገናኝተው ወደፊት ትብብር ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መወያያታቸው ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዳያስፖራው ጋር ከሚያደርጉት ውይይት በተጨማሪ በፍራንክፈርት ማዘጋጃ ቤት ተገኝተው የክብር ፊርማቸውን ያኖራሉ።