ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዲስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ተሰየመ

አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዲሱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ተሾሙ፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂኒየር ጌታሁን መኩሪያ፣ የትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት አቶ አበበ አበባየሁ እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ ከመንግስት ወገን የቦርዱ አባላት ሆነው የተሰየሙ ናቸው። ከምርት ገበያው አባላት ደግሞ አቶ አብደላ አቡበከር ባገርሽ፣ አቶ አሉላ ገብረሚካዔል፣ አቶ ቡልቡላ ቱሌ፣ አቶ አበባው አንዳርጌና አቶ ዑመር ዋቢ አባል በመሆን ተሰይመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የዳይሬክተሮች ቦርድ 11 አባላት ሲኖሩት ሊቀ መንበሩን ጨምሮ ስድስቱ አባላት በመንግስት የሚሰየሙ ሲሆን የተቀሩት አምስቱ ደግሞ በምርት ገበያው ደንብ መሰረት በምርት ገበያው አባላት ይመረጣሉ። ቦርዱ የምርት ገበያውን በበላይነት እንደሚቆጣጠር በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅ ተደንግጓል፡፡ የምርት ገበያው ለሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ቀሪ ሁለት ዓመታት ሥራ ላይ የሚውል የስትራቴጂ ክለሳ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል። የምርት ገበያው የሥራ አድማሱን በማስፋት የተለያዩ አዳዲስ ሥራዎችን ለመስራትና ለውጭ ምንዛሬ እድገት ጠንክሮ እንዲሰራ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሹመቱ እንደሚያግዘው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አሰፈፃሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ ገልጸዋል። የሥራ ጊዜውን ያጠናቀቀው የቀድሞው የዳይሬክተሮች ቦርድ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ ለነበረው የላቀ አስተዋጽኦ ዋና ስራ አስፈጻሚው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው አዲሱ ቦርድ ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በመጠቆም ለአዲሱ የቦርድ አመራር መልካም የሥራ ጊዜን ተመኝተዋል፡፡ የአዲሱ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ይናገር ደሴ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ እንደነበሩ አስታውሰው የወጪ ንግድን ለማገዝ የተጣለባቸውን አገራዊ ሐላፊነት ለመወጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም