አገር አቀር የሴቶች የሰላም ኮንፈረንስ የማህበረሰብ ንቅናቄ በመጪው ሰኞ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀር የሴቶች የሰላም ኮንፈረንስ የማህበረሰብ ንቅናቄ በመጪው ሰኞ ይጀምራል
አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2011 አገር አቀር የሴቶች የሰላም ኮንፈረንስ የማህበረሰብ ንቅናቄ በመጪው ሰኞ እንደሚጀምር የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ። "ሴቶች ዘረኝነትን በመጠየፍ ለሰላም ግንባር ቀደም ሚናችንን እንወጣለን'' በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የሰላም ኮንፈረንስ በማስመልከት ሴት ሚኒስትሮች በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ስጥተዋል። መድረኩ ሴቶች በአገሪቷ ሰላም በዘላቂነት ለማረጋጋጥ በሚያበረክተው አስተዋጾ ላይ ትኩረት ለመስጠት ጀግንነታቸውን የሚያሳዩበት ነው ተብሏል። በኮንፈረንሱ 800 የሚደርሱ ከፌዴራልና ከሁሉም ክልል የተወጣጡ ሴቶች ተሳታፊ ይሆናሉ። የሰላም ኮንፈረንሱ ዓላማ የኢትዮጵያ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች በግጭትና ተያየዥ ችግሮች ላይ ያላቸውን ተጋላጭነት በመቀነስ የመብት ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማስቻል እንደሆነ ተገልጿል። የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ወይዘሮ የአለም ጸጋዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሴቶች በእናትነታቸው ከቤታቸው ጀምሮ አካባቢቸውንና አገራቸውን ከመለያየትና ከግጭት የሚከላከሉበት ክህሎትና ልምድ ያላቸው በመሆኑ ለሰላም መስፈን ሚናቸውን እንዲወጡ ኮንፈረንሱ መነቃቃት ይፈጥራል። በኮንፈረንሱ የፌዴራልና ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ሴቶች ስለ ሰላም በዘላቂነት በህብረት ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸው ስራዎች ለማከናወን የሚረዳ የሰላም ጥምረት እንደሚመሰርቱ ተናግረዋል። የሰላም ጥምረቱ ዋናው ዓላማው ሴቶች ሰላም አስመልክቶ በጋራ የሚያቅዱበትና የሚወያዩበት፤ ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር ለዘላቂ ሰላም ለማስፈን በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል ነው። በኮንፈረንሱ በተላዩ ዘርፎች በኃለፊነት ደረጃ የሚገኑ ተጽህኖ ፈጣሪ ሴቶች ለተተኪ ወጣቶችና ህጻናት ኣረኣያ የሚሆኑበት መድረክ የሚፈጠር ''ጀግኒት" በሚል መጠሪያ የተዘጋጀ ሰፊ የማህበረሰብ እንቅስቃሴ ፕሮግራም በይፋ ይጀመራል ተብሏል።