ቀጥታ፡

የእግር ኳስ ሜዳዎችና ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት በመዲናዋ ያለውን የእግር ኳስ እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዳከመው መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2011 የእግር ኳስ ሜዳዎችና ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት በመዲናዋ ያለውን የእግር ኳስ እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዳከመው መምጣቱ ተገለጸ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግና ብሔራዊ ሊግ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ደጋፊዎች ጋር በአዲስ አበባ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ላይ ዛሬ ውይይት አድርገዋል። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ክፍሌ ወልዴ አዲስ አበባ በታሪኳ ብዙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና ሜዳዎች እንደነበሯትና ከዚያም ተዋቂ ተጫዋቾች መውጣታቸውን አስታውሰዋል። አሁን ግን በመሰረተ ልማት ግንባታዎች የእግር ኳስ ሜዳና የማዘውተሪያ ስፍራዎች በአሳሳቢ ሁኔታ በመቀነሳቸው በአዲስ አበባ ያለውን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ እያዳከመውና ተተኪ ተጫዋቾች እንዳይፈጠሩ እያደረገ ነው ብለዋል። በተለይም ወጣቱ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ በማጣቱ ምክንያት አልባሌ ቦታዎች በመዋል ለሱስ እየተደረገ እንደሆነና ከተማ አስተዳደሩ በፍጥነት አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ገልጸዋል። እግር ኳስ ከፖለቲካ ፣ ሃይማኖትና ዘር የጸዳ ስፖርት እንደሆነና በአሁኑ ሰዓት ወደ ብሔርና ፖለቲካ መልኩን እየቀየረ መምጣቱንና ይህም ከወዲሁ መፍትሔ ካልተሰጠው እግር ኳስን መጫወት ሳይሆን ማሰብም እንደሚከብድ ተናግረዋል። ከተማ አስተዳደሩ ከክልሎች ጋር ተባብሮ በመስራት የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶችንና ከብሔርና ከፖለቲካ ጋር የሚነሳውን ጉዳይ መፍታት እንዳለበትም ነው አቶ ክፍሌ ያስረዱት። በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚመደቡ የጸጥታ አካላት ከደጋፊዎች ማህበር አስተባባሪዎች ጋር በቅርበት መስራት እንዳለባቸው ያስረዱት አቶ ክፍሌ፤ አንዳንድ የጸጥታ አካላት ደጋፊዎችን ያለ አግባብ እየደበደቡ እንደሆነና ይህም ሊታረም እንደሚገባ ነው የተናገሩት። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አቶ ምንሊክ ግርማ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ክለቦች ወደ ክልል ሄደው በሚጫወቱበት ወቅት ለሚደርስባቸው ጉዳት የከተማ አስተዳደሩ በዝምታ እንደሚያልፍና ጥበቃ እየተደረገላቸው እንዳልሆነም ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደሩ ለአዲስ አበባ ክለቦች ጥበቃ ሊያደርግ እንደሚገባና በዚህ ጉዳይ ላይ መፍትሔ እንዲሰጥበትም ጠይቀዋል። ክለባቸው እንደ ታሪካዊነቱና ለእግር ኳሱ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ አንጻር የከተማ አስተዳደሩ ምንም አይነት እውቅና እንዳልሰጠውና ያገኘውም ጥቅም እንደሌለ ገልጸዋል። ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በአዲስ አበባ የእግር ኳስ ሜዳዎችና ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት ዙሪያ ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል። የአዲስ አበባ ክለቦች በኢትዮጵያ የክለብ ውድድሮች ያላቸው ተሳትፎ እየቀነሰ መምጣቱንና መዳከማቸው እየታወቀ ከተማ አስተዳደሩ "ምንድነው ችግራችሁ?" ብሎ አለመጠየቁ ትክክል እንዳልሆነም ተጠቁሟል። ለዚህም የውይይት መድረኮች ቀጣይነት ሊኖራቸው ይገባል፤ ውይይቱ በአገር አቀፍ ደረጃ መስፋት አለበት፤ ሚዛናዊ የሚዲያ አዘጋገብ ችግር አለበት፤ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር የሚፈታ ኮሚቴ ቢቋቋም የሚሉና ሌሎችም በውይይቱ ላይ የተነሱ ሀሳቦች ናቸው። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በተለያየ ምክንያት ተይዘው የነበሩና ከተማ አስተዳዳሩ ያስመለሳቸው መሬቶች ለልማት እንደሚውሉና ይሄም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራና የወጣት ማዕከላት እንደሚካተቱበት ገልጸዋል። በተለይም ወጣቱ የሚውልበት፣ የሚዝናናበትና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርግባቸው ስፍራዎች እንዲሰፉ ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በአጠቃላይ የሜዳዎችና የማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲበዙና ተደራሽነታቸው እንዲሰፋ ከተማ አስተዳደሩ ያደርጋል ብለዋል። ለአዲስ አበባ ክለቦች የሚያስፈልገው ድጋፍ እንደሚደርግና ከተማ አስተዳደሩ ከክለቦችና ከደጋፊዎች ማህበሮች ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ነው ምክትል ከንቲባው ያስረዱት። በእግር ኳሱ ላይ እየታየ ያለውን የብሔርና የፖለቲካ ጉዳይ የአዲስ አበባ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ጋር ጥሩ ስራ በመስራት ለክልሎችም አርአያ መሆን እንችላለን፤ ከክልል የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት በማድረግም ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ጥረት ይደረጋል ብለዋል። እግር ኳሱ መሰረት ማድረግ ያለበት ኢትዮጵያዊነት ላይ እንደሆነና ሁሉም በዚያ መነጽር ከታየ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚቀልም ተናግረዋል። ከተማ አስተዳደሩ በውይይቱ የተነሱ ሀሳቦችን እንደ አደራ እንደማይመለከታቸውና ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠትና መስራት የተሰጠን ሃላፊነት ነው ብለዋል ምክትል ከንቲባው። የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባ እግር ኳስን በማሳደግና ችግሮችን በመፍታት መልካም ገጽታ መገንባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በእግር ኳሱ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ክለቦች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የጸጥታ አካላት፣ ደጋፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡም ምክትል ከንቲባው ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ውይይቶቹ ቀጣይነት እንደሚኖራቸውና የሚነሱ ጉዳዮችን በዘርፍ በመከፋፈል በቀጣይ ዝርዝር ውይይት እንደሚደረግባቸውም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም