የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ተጠቃሚዎች አብዛኞቹ ሳይከፍሉ እንደሚገለገሉ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ተጠቃሚዎች አብዛኞቹ ሳይከፍሉ እንደሚገለገሉ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2011 በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት የትኬት ቁጥጥር ስለማይደረግ አብዛኛው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ሳይከፍሉ እንደሚጓዙ ተጠቃሚዎች ገልጹ። ኢዜአ ባደረገው ምልከታም ቁጥጥር እየተደረገ እንዳልሆነ መታዘብ ችሏል። የገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት ኢንጂነር ሰለሞን ፀጋየ ትኬት ሳይቆርጡ ተሳፍረው የሚጓዙ መኖራቸውን ታዝበው በትኬት ቆራጮች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ቢደረግ መልካም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የቁጥጥር ሙከራዎች ቢኖሩም ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ የለም፤በመሆኑም መስትሔ ሊበጅለት ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ ዲነግዴ ደራራ ናቸው ፡፡ አቶ አስራቴ ኃይሉ እንዳሉት ተሳፋሪው ለህሊናው ብሎ የሚከፍል ካልሆነ በስተቀር ቁጥጥር የማይደረግ በመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሌላው አቶ መስፍን ኃይሌ በበኩላቸው ትኬት ሳይቆርጡ ወደባቡሩ ገብተው የሚሳፈሩና ባለ ሁለት ብር ትኬት ቆርጠው የስድስት ብር ተመን ያለው ርቀት የሚጓዙ እንዳሉም ጠቁመው ይህ ደግሞ ለካምፓኒው ጉዳት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ የተሳፋሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆን የትኬት ቁጥጥር ስራ እንዳይከናወን ማድረጉን ተናግረዋል። ችግሩን ለመፍታት ጥናት ተደርጎ ለሚመለከተው አካል መቅረቡን ጠቁመዋል። ችግሩን ለመፍታት የተለያየ መፍትሄ መቀመጡን የተናገሩት አቶ ደረጀ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ አገልግሎት ሰጪዎችን በማሰማራት ቁጥጥር ለማድረግ በጎ ፈቃደኞችን ከየክፍለ ከተማው የምስገባ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። አብዛኛው ተገልጋይ ሳይከፍል የሚጠቀምበት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎቱ ገቢ ከወጪው ያነሰ መሆኑን ከምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል። በዚህ የተነሳ ወጪውን ለመሸፈን በየዓመቱ ከከተማ አስተዳደሩ የገንዘብ ድጎማ ይደረግለታል። የሚገኘውን ገቢ ከወጭው ጋር ለማመጣጠን እንዲያስችል በለገሐር፣ በልደታ፣ በዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይና በአውቶብስ ተራ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች ለመገንባት መታቀዱን አቶ ደረጀ ጠቁመዋል። ከቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መንግስት ማግኘት ያለበትን ገቢ ሊያሳጣው አይችልም ወይ? በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው የባቡር አገልግሎቱ ለትርፍ አለመቋቋሙን ጠቅሰው ህብረተሰቡ ለህሊናው ሲል ከፍሎ ሲጓዝ መፍትሄ እንደሚገኝ ተናግረዋል።