ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተላቀን ከወንዶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነናል - የሰመራ ሎግያና ዱብቲ ወረዳ ሴቶች - ኢዜአ አማርኛ
ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተላቀን ከወንዶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነናል - የሰመራ ሎግያና ዱብቲ ወረዳ ሴቶች
ሰመራ ግንቦት 14/2010 ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተላቀው ከወንዶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ በአፋር ክልል አስተያየታቸውን የሰጡ የሰመራ-ሎግያና ዱብቲ ወረዳ ሴቶች ገለጹ፡፡ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል፡፡ በዱቡቲ ወረዳ የአስቦዳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፋጡማ አልሃምዱ በሰጡት አስተያየት በክልሉ በስፋት ይካሄድ በነበረው አስከፊ የሴት ልጅ ግርዛት ሰለባ በመሆናቸው በተለይም በወሊድ ጊዜ ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ መንግስት ይህንን ጨምሮ በክልሉ የሚታዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ባደረገው ጥረት የህብረተሰቡ አስተሳሰብ እየተለወጠ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት ችግሩ በመቃለል ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እሳቸውም ያሏቸውን ሦስት ሴት ልጆች እንዳይገረዙ በማድረግ በቀጣይ ሊደርስባቸው ከሚችለው የጤና ችግር መታደጋቸውን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም በነበረው ባህላዊ ተጽእኖ ያጡትን የትምህርት እድል ልጆቻቸው እያገኙ በመሆናቸው የወደፊት ህይወታቸው የተሻለ እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ባለቤት በመሆን ከባለቤታቸው ጋር እኩል የመወሰንና የማስተዳደር መብት ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በሎግያ ከተማ በሆቴል ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ዘነበች አብረሃ በበኩላቸው መንግሰት ሴቶች ከባህል ተጽእኖ ተላቀው ሰርተው ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ በፈጠረው መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በ1991 አ.ም በከተማ አነስተኛ ምግብ ቤት ከፍተው ስራ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡ ስራቸው በሂደት አድጎ ዛሬ በከተማው ከሚጠቀሱ ትላልቅ ሆቴሎች አንዱ ለመሆን እንደበቃ ተናግረዋል፡፡ ይህም ከእሳቸው የግል ጥረትና ጥንካሬ ባለፈ ባለቤታቸው ሴት ከጓዳ ወጥታ ሰርታ መለወጥ ትችላለች የሚለውን ሃሳብ ተቀብሎ ድጋፍ ስላደረጉላቸው ጭምር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ያደረገላቸው የመስሪያ ቦታና ተያያዥ ድጋፍ ለአሁኑ ስኬታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የሰመራ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ነስሮ ኡዳ በክልሉ በስፋት ይፈፀም በነበረው የሴት ልጅ ግርዛትና ያለእድሜ ጋብቻ ታላላቅ እህቶቿ ሰለባ መሆናቸውን ገልፃለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በተከናወነው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የቤተሰቦቿ አስተሳሰብ በመቀየሩ ከችግሩ ነፃ ሆና ታላላቅ እህቶቿ ያጡትን የመማር አድል በማግኘት ሁለተኛ ዲግሪ መያዟን ተናግራለች፡፡ በዚህም በመንግሰት ስራ ላይ ተሰማርታ በመስራት ላይ መሆኗል ገልፃ ያለማንም ተጽእኖ በራሷ ፍቃድ ከመሰረተችው ትዳር ልጆች ወልዳ ደስተኛ ህይወት እየመራች መሆኑን አብራርታለች፡፡ የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዘሃራ መሃመድ ባለፉት አመታት ተግባራዊ በመደረግ ላይ ባለው ፌደራላዊ ስርዓት የክልሉ ሴቶች እንደሌሎች ክልል ሴቶች ሁሉ ሰብአዊና ዴሞክራሲዊ መብታቸው ተረጋግጦ በሁሉም መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው፡፡ የክልሉ ሴቶች በየአካበቢቸው በተሰሩ የጤናና ትምህርት እንዲሁም የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ከመሬት ባለቤትነት ጀምሮ እስከ ትልልቅ ኢንቨስትመንት መስክ ተሳታፊ በመሆን የራሳቸውን ሃብት በማፍራት ኑሯቸውን እያሻሻሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በፖለቲካው መስክም በየደረጃው በሚገኙ የአመራርና ኃላፊነት በተጨማሪ እራሳቸውን በእውቀትና ክህሎት እየገነቡ በመምጣታቸው በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ተመድበው የክልሉን ልማት ከመደገፍ ባለፈ እራሳቸውንም ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የእስካሁኑ የሴቶች ተሳትፎ አበረታች ቢሆንም ከሚፈለገው ደረጃ አንጻር ገና ብዙ ሰራዎች እንደሚቀሩ ተናግረዋል፡፡ በህገመንግስቱ የተረጋገጡ የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን በተሟላ ሁኔታ ስራ ላይ በማዋል ድህነትን ለማሸነፍ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጠል ተናግረዋል፡፡