ቀጥታ፡

የኤክስፖርት ቄራዎችን ፍላጎት በማሟላትና አቅማቸውን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዳማ ጥቅምት 20/2011 የኤክስፖርት ቄራዎችን የአቅርቦት ፍላጎት በማሟላትና አቅማቸውን በማሳደግ ከዘርፉ ተገቢውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ። ኢንስቲትዩቱ በተያዘው የበጀት ዓመት ሥጋ፣ ወተት፣ ማርና ሠም ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመላክ ከ198 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማስገኘት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስታውቋል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ጉታ ለኢዜአ እንደገለጹት የእንስሳት ሀብት ልማት፣ አረባብና አያያዝን በማሻሻል የኤክስፖርት ቄራዎችን ፍላጎት በጥራትም ሆነ በብዛት ለማሟላት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው። ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት እስከ 2ሺህ ቶን የሚደርስ ሥጋ አርደው ኤክስፖርት ማድረግ የሚችሉ ቄራዎች ወደ ሥራ ገብተዋል። ኢንስቲትዩቱ በሥራ ውስጥ ያሉ 14 የኤክስፖርት ቄራዎችን የአቅርቦት ፍላጎት በማሟላት በሙሉ አቅማቸው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። እንስሳቱን በሚፈለገው ጥራትና ብዛት ማቅረብ አለመቻል የዘርፉ ቁልፍ ችግሮች እንደሆኑ መለየታቸውን ጠቅሰው " ችግሮቹን በመፍታት አቅርቦቱን ለማሳደግ በየደረጃው ከሚገኙ የግብርናና እንስሳት ሴክተር ተቋማትና በዘርፉ ከተሰማሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው" ብለዋል። በተለይም እንስሳትን በማድለብ የተሰማሩ ማህበራት የኤክስፖርት ቄራዎች የሚፈልጉትን በጎች፣ ፍየሎችና የዳልጋ ከብት በጥራትና በብዛት እንዲያቀርቡ በቂ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ከእዚህ በተጨማሪ ደረጃቸውን የጠበቁ የእንስሳት ማድለቢያዎችና ተያያዥ ችግሮቻቸው በፍጥነት የሚፈቱበትና ምላሽ የሚያገኙበት አሰራር ለመዘርጋት በጋራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ከሥጋ፣ ወተት፣ ማርና ሰም የወጪ ንግድ ከ198 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማስገኘት ታቅዶ ከወዲሁ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ታደሰ ተናግረዋል። በ2010 በጀት ዓመት ከ20 ሺህ ቶን በላይ ስጋ፣ ማር፣ ሰምና ወተት ወደ ተለያዩ የመካክለኛው ምስራቅና አውሮፓ ሀገራት በመላክ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ከዘርፉ መገኘቱንም አስታውሰዋል። የሀገር ውስጥ እንስሳት ዋጋ በውጭ ሀገር ከሚሸጠው መብለጥ፣ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎች መስፋፋት፣ በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት የአቅም ውስንነትና የአሰራር ኋላቀርነት የኤክስፖርት ቄራዎችን እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በግብርናና እንስሳት ሀብት ሚንስቴር የኤክስፖርት ቄራዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ጌዲዮን ይልማ ናቸው። " የሥጋ ምርት ጽዳትና ጥራት መጠበቅ፣ የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ሥርዓቱን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማሻሻል እንዲሁም የመኖ አመራረትና አዘገጃጀት ብቁ በሆኑ ባለሙያዎች እንዲዘጋጅ በማድረግ ጥራቱ የተጠበቀ ምርት መላክ ይገባል" ብለዋል። ይህን ለማድረግ የሰለጠኑ ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት በዘርፉ በስፋት ከማሳተፍ በተጨማሪ በኤክስፖርት ቄራ የተሰማሩ ባለሃብቶችም በእንስሳት እርባታና ማድለብ ሥራ እንዲሰማሩ የመሬትና የብድር አገልግሎት በፍጥነት ማመቻቸት እንደሚገባ አስረድተዋል። "ከእዚህ በተጨማሪ የጤና ሙያተኞችን ብቃት ማጎልበት፣ የህክምና የምርምር ማዕከላትን አቅም ማጠናከር፣ የክትባት፣ የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦትና አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል። የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ገብረዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው የኤክስፖርት ቄራዎችን እያጋጠመ ያለው የአቅርቦት ችግር መንስኤ የእንስሳት ሀብቱ በህገ ወጥ መንገድ በኮንትሮባንድ ከሀገር መውጣት መሆኑን አስረድተዋል። "ይህን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት የፖሊስና የህግ ማዕቀፎችን አዘጋጅተን ከማጽደቅ ባለፈ ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፈን ሀገራዊ ንቅናቄ ጀምረናል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም