የርብ መስኖ ፕሮጀክት የካናል ስራ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ምርት መግባት እንፈልጋለን--- የአካባቢው አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የርብ መስኖ ፕሮጀክት የካናል ስራ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ምርት መግባት እንፈልጋለን--- የአካባቢው አርሶ አደሮች
ባህርዳር ጥቅምት 19/2011 የርብ መስኖ ፕሮጀክት ቀሪ የካናል ዝርጋታ ስራዎች ተጠናቀው ወደ መስኖ ልማት እንዲገባ የሚመለከታቸው አካላት ተባብረው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ጠየቁ። የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር አርሶ አደሮቹ በፍጥነት ወደ ማምረት ስራ እንዲገቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጀት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡ በዞኑ የፎገራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት "ወደ ስራ መግባት እንድንችል የርብ መስኖ ፕሮጀክት ቀሪ የካናል ስራዎች በፍጥነት ሊጠናቀቁ ይገባል" ብለዋል፡፡ በወረዳው ድባ ድልድይት ቀበሌ ነዋሪ አስር አለቃ ተዘራ በላይ ባለፉት አመታት በአካባቢያቸው የሚገኘውን አነስተኛ የምንጭና የወንዝ ውሃ በመጥለፍ በመስኖ ስራ ሲያለሙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ በሚቆየው የውሃ እርጥበት በመጠቀም ሩዝ፣ ሽምብራ፣ አጃና ጓያ በማምረት ተጠቀሚ መሆናቸውን የጠቆሙት አርሶ አደሩ አመቱን ሙሉ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችን ለማምራት የውሃ እጥረቱ እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል። የርብ መስኖ ፕሮጀክትን ለመጠቀም ከሁለት ዓመት በፊት ጀምረው ዝግጅት ቢያደርጉም የካናል ዝርጋታው ባለመጠናቀቁ እስከ አሁን ምንም ጥቅም ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸው "ካናሉ ተጠናቆ ወደ ስራ ከገባ በአመት እስከ ሦስት ጊዜ የምናመርትበት እድል ይፈጠራል" ብለዋል፡፡ በዚሁ ወረዳ የወበሌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጎበዜ መንግስት በበኩላቸው በባህላዊ የመስኖ ልማት በየአመቱ ከ50 ኩንታል በላይ የአጃ ምርት እንደሚያገኙ አስታውሰዋል። አትክልትና ፍራፍሬን በአመት ሶስት ጊዜ ለማምረት ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት አርሶ አደሩ በውሃ እጥረት ምክንያት የሚጠብቁትን ያህል ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል። የርብ የመስኖ ፕሮጀክት የተሻለ የመስኖ ልማት ለማካሄድ ትልቅ ተስፋ እንደሆናቸውና በጉጉት እየጠበቁት እንደሚገኙም አብራርተዋል። በመሆኑም እንደ ውሃ ማጠራቀሚያው ሁሉ የካናል ዝርጋታው በፍጥነት ተጠናቆ አርሶ አደሩ ወደ ማምረት እንዲገባ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል። የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ዳምጤ የርብ መስኖ ግንባታው መጠናቀቅ ከነበረበት ስድስት ዓመታትን ዘግይቶም ለምርቃት መብቃቱን ተናግረዋል፡፡ በተጠራቀመው ውሃ የዓሳ እርባታ በመጨመር ወጣቶችን በዘርፉ አደራጅቶ ለማሰማራት የምልመላና መረጣ ስራ መከናወኑን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው በቅርቡም ወደ ማምረት እንደሚገቡ ገልጸዋል። በእብናትና ፋርጣ ወረዳዎች መካከል የተገነባው ፕሮጀክቱ ከ90 በመቶ በላይ ተጠናቋል ያሉት አስተዳዳሪው አሁን ወደ ልማት የሚያስገባ የካናል ስራ እንዳልተጠናቀቀ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ሦስት ሺህ ሄክታር መሬት ወደ ልማት ለማስገባት የመለየት ስራ ቢከናወንም ግንባታው በመዘግየቱ ማስጀመር አለመቻሉን ጠቁመው፤ በዚህ ዓመትም 5 ሺህ ሄክታር መሬት የመለየት ስራ ለመስራት ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል። ይሁን እንጂ የካናል ዝርጋታ ስራው ከሚጠበቀው በላይ በመዘግየቱ በዚህ ዓመት ወደ ስራ ይገባል ተብሎ እንደማይጠበቅ አመልክተው፤ ችግሩ በፍጥነት እንዲፈታም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአርሶ አደሮቹ ጥያቄ ትክክል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሲሳይ "መንግስት የችግሩን አንገብጋቢነት በመገንዘብ በልዩ ትኩረት እንዲጠናቀቅ ከሚመለከተቸው አካላት ጋር ይሰራል" ብለዋል። የርብ መስኖ ፕሮጀክት234 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን ከ28 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 20 ሺህ ሄክታር መሬት ያለማል ተብሎ ይጠበቃል።